“በየአቅጣጫው ጦር የሰበቁ ኀይሎችን ታሪክ አድርገን በድል ሕልውናችንን እናስጠብቃለን” ዓለም-አቀፍ የአማራ ንቅናቄ

804

“በየአቅጣጫው ጦር የሰበቁ ኀይሎችን ታሪክ አድርገን በድል ሕልውናችንን እናስጠብቃለን” ዓለም-አቀፍ የአማራ ንቅናቄ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም-አቀፍ የአማራ ንቅናቄ የፌዴራል መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የሚነዙ
ወሬዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ
ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ፖለቲካዊ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎም የአሸባሪው ህወሃት አባላት በአማራ
ሕዝብ ላይ ጦርነት እንደሚከፍቱ በዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ ማወጁን ነው ንቅናቄው በመግለጫው ያሳወቀው፡፡
የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በደምና በአጥንቱ ጠብቆ ባቆያት ሀገሩ ከሃዲዎች ባሳረፉበት የጭቆና ቀንበር
ከርስቱ ሲፈናቀል፣ ሲሳደድ፣ ሲገደልና በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይገባው አሰቃቂ ድርጊት ሲደርስበት ዓመታት ማለፋቸውን
አስታውሷል፡፡
ስለሚሳሳላት ኢትዮጵያ ያን ሁሉ መከራ ችሎ ቢያሳልፍም ጠላቶቹ እንቅልፍ አጥተው በተቀናጀ አግባብ ዘመቻ ማድረጋቸውንም
አንስቷል፡፡ ምንም እንኳን ሆደ ሰፊነት፣ አስተዋይነትና ፍርድ አዋቂነት የአማራ ሕዝብ ታላቅ ዕሴቶች ቢሆኑም ለሚቃጣበት ጥቃት
ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው አስታውቋል፡፡
በአማራ ሕዝብ ላይ ለተጎሰመው የጦርነት ነጋሪት ከፍተኛ ግምት በመስጠት ሁሉም አማራ በአንድነት ሁሉን አቀፍ ዝግጅት
ማድረግ አለበት ብሏል፡፡ የተቃጣበትን ጥቃት ስፋትና ጥልቀት በሚገባ ተገንዝቦ በአንድነት የሚቆምበት፣ የሚደጋገፍበት፣ አንዱ
ለሌላው ተገን የሚሆንበት ወሳኝ ጊዜ እንደሆነም አስገንዝቧል፡፡
ንቅናቄው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው የጠላት ሴራ የአማራ ሕዝብ አንድ እንዳይሆን መከፋፈል
ነው። ሕዝቡ ራሱን ሊያድን የሚችለው ተባብሮ መቆም ሲችል ነውና አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር አካባቢውን ነቅቶ
እንዲጠብቅም አሳስቧል፡፡ በአንድ ሃሳብ፤ በአንድ ልቦናና በአንድ ዓላማ ከተሰለፍን የማንሻገረው የታሪክ አቀበት አይኖርም ያለው
ንቅናቄው “በየአቅጣጫው ጦር የሰበቁ ኀይሎችን ታሪክ አድርገን በድል ሕልውናችንን እናስጠብቃለን!” ብሏል፡፡
ከሰሞኑ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በመግለጫውም ወልቃይት፣
ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋእትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን አሳውቋል፡፡ እነዚህን
አካባቢዎች በጉልበት የመጠቅለል ፍላጎት ካለ፣ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌለ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሸባሪው ትሕነግ ለሀገር አስጊ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ሁለት ተሰጡ ሁለቱንም ሰጡ”
Next article“የፌዴራል መንግሥት የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይዟል” የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ