
“እጅህን በእኛ ላይ እንዳነሳህ እናውቃለን፤ የሙያ ብቃትህ ግን ለሀገር ስለሚጠቅመን ወደ ሥራህ ብትመለስ እንፈቅዳለን” አፄ ኃይለ ሥላሴ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የቆሎ ተማሪ፣ የክቡር ዘበኛ የጦር መኮንን፣ የኢትዮያ የባህር ኃይል መስራችና ምክትል አዛዥ፣ የኮርያ እና ኮንጎ የሰላም ማስከበር ዘመች መሪ እና ተሸላሚ መኮንን፣ ዲፕሎማት እና ጉምቱ ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡ ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የሀገር እና ሕዝብ አገልጋይነታቸው የጦር መኮንን እና በተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በሀገራቸው ኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ዘንድ ታሪክ የማይዘነጋ አስደናቂ ገደሎችን ፈጽመው አልፈዋል፤ ኮሎኔል ዕምሩ ወንዴ፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፓለቲካና ወታደራዊ ታሪክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ኮሎኔል ዕምሩ ወንዴ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትላበስ በሕይወት ዘመናቸው ኹሉ ታትረዋል፡፡ በ1953 ዓ.ም የተሞከረው መፈንቀለ መንግሥት ከከሸፈ በኋላ በስፋት ሲነገር የማንሰማውን የ1956 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኮሎኔል እምሩ ወንዴ የተመራ ነበር፡፡
ኮሎኔል ዕምሩ ወንዴ በዘመኑ በነበረው አጠራር በበጌ ምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት በደብረ ታቦር አውራጃ “አትከና ጊዮርጊስ” በ1924 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በተወለዱበት አጥቢያ በአትከና ጊዮርጊስ እና ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ግብረ ዲቁና እና የዜማ ትምህርት ተምረዋል፡፡ በአብነት ትምህርት ቤት ያገኙት እውቀት በኋላ ላይ ለደረሱበት ትልቅ ቦታ መሠረት ሆኖ እንዳገለገላቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ መጠይቅ በተደጋጋሚ ያነሱታል፡፡
የቆሎ ተማሪው ዕምሩን ፈጣን የትምህርት አቀባበል ያዩት በአዲስ አበባ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የነበሩት አጎታቸው ፊታ አውራሪ ጸጋዬ ቸኮል በ1937 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አምጥተው በዘመኑ ዝነኛ ከነበረው የዳግማዊ ምኒልክ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቧቸው፡፡ በትምህርታቸውም ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው ደግሞ በትምህርት ቤቱ ከሚታወቁት ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ለመሆን ቻሉ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሚያዝያ 7/1938 ዓ.ም በትምህርታቸውና በአካል ብቃታቸው ተመርጠው ለክቡር ዘበኛ የጦር አካዳሚ “ለዕጩ መኮንንነት” ስልጠና ተላኩ፡፡
በማሠልጠኛው የሚሠጠውን እና ለመስመራዊና ለከፍተኛ መኮንንነት የሚያበቃውን የሦስት ዓመታት የወታደራዊ ሣይንስ ትምህርት በማጠናቀቅ “በምክትል የመቶ አለቅነት” ማዕረግ በመስከረም ወር 1941 ዓ.ም ተመረቁ፡፡
በክቡር ዘበኛ መኮንንት ለአራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላም ወታደራዊ ጥበበኛው መቶ አለቃ ዕምሩ በ1945 ዓ.ም ከፍ ላለ ወታደራዊ ትምህርት ወደ አሜሪካ ካዴት ወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ቤት አቀኑ፡፡ በወቅቱ ሀገሪቱ ካፈራቻቸው እና ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ውጭ ከላከቻቸው ወጣት ምርጥ 10 መኮንኖች አንዱ ለመሆን በቁ፡፡ በቆይታቸው ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የሚሰጠውን የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት አጠናቅቀው ከተመረቁ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ከውጭ ትምህርት መልስ ሻምበል የሚል ማዕረግ ያገኙት ጥበበኛው ወታደር ለሌላ ከሀገር ያለፈ የታሪክ አሻራ ዕድል በሯን ከፈተችላቸው፤ ሻምበል ዕምሩ የኮሪያ ዘማች ሆኑ፡፡
ከ1951 እስከ 1952 ዓ.ም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ካሰማራችው ሠራዊት መካከል አንዱ የነበሩት ሻምበል ዕምሩ በኮሪያ በነበራቸው ቆይታ የመጀመሪው ኃላፊነታቸው በቃኘው ሻለቃ እና በአሜሪካ 32ኛው ሬጅምንት አገናኝ መኮንንነት የማስተባበር ሥራ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ ደግሞ የሻለቃው የሥልጠና እና የዘመቻ መኮንን በመሆን እጅግ አመርቂ ሥራ በማከናወን ለቃኘው ሻለቃ ትልቅ ስኬት ልዩ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
ሻምበል ዕምሩ በነሐሴ 1952 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ የመኮንኑን ክህሎት በማድነቅ 3ኛ ቃኘውን እንዲያሰለጥኑ አደረጓቸው፡፡ ሻምበል ዕምሩም በኮሪያ የውጊያ ቆይታቸው ባዳበሩት የጦር እውቀት ላይ በመመርኮዝ በሰጡት ሥልጠና የቃኘውን አገልግሎት በልዩ ችሎታቸው አዳብረውታል፡፡
ሥልጠናው ሲጠናቀቅም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩቅ ምሥራቅ ወታደራዊ እዝ የኢትዮጵያ ቡድን መሪ ሆነው ተሾሙ፡፡ በኮሪያ ልሳነ ምድር ስለተደረገው ከባድ ጦርነት የሚያትተው እና በሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተዘጋጅቶ በተሰነደው መጽሐፍ ውስጥ ዘመቻውን የተሳተፉ ሀገሮች እና ጀብዱ የሠሩ የጦር መኮንኖች መካከል ግንባር ቀደም የጦር መኮንን በመሆን ስማቸው ተቀምጧል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥም ይህን ኢትዮጵያዊ የጦር መኮንን በሚመለከት እንዲህ ይላል “ይኽ ወጣት የጦር መኮንን በጣም ብሩህ አዕምሮ ያለው፣ አስተዋይ እና ከፍተኛ እምነት የሚጣልበት ነው፡፡ ወደፊትም ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት እና ተስፋ የሚጣልበት መኮንን መሆኑን ስንመሰክር በታላቅ ኩራት ነው” የሚል ነበር፡፡
በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊነቶች ያገለገሉት ኮሎኔል ዕምሩ ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል የሚል የጸና አቋም ስለነበራቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ገቡ፡፡ በመጨረሻም ብዙም ያልተወራለትን የ1956 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲያደርጉ መረጃው ቀድሞ ለንጉሠ ነገሥቱ በመድረሱ በቁጥጥር ስር ውለው የ15 ዓመታት እስር ተበየነባቸው፡፡ የኮሎኔል እምሩ መታሰር ሀገርን በብዙ ይጎዳል የሚል ተደጋጋሚ ምክረ ሐሳብ የደረሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ “እጅህን በእኛ ላይ እንዳነሳህ እናውቃለን፤ የሙያ ብቃትህ ግን ለሀገር ስለሚጠቅመን ወደ ሥራህ ብትመለስ እንፈቅዳለን” አሏቸው፡፡
የንጉሡን ምሕረት ተቀብለው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በደጃዝማች ዶክተር ዘውዴ ገብረ ሥላሴ አማካኝነት የተመከሩት ኮሎኔል ዕምሩ “ጃንሆይ የተፋሁትን መልሼ አልሰውም” በማለት ወደ ወታደራዊ ሥራው የመመልሱን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ከተፈቀደላቸው የጡረታ ዋስትና ጋር ነጻ ወጥተው በፊሊፕስ ኩባንያ ለጥቂት ዓመታት ሠሩ፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ የዘውድ ዘመን አልቆ ደርግ መንበረ ስልጣኑን ቢቆጣጠርም ኮሎኔል ዕምሩን ያምፃሉ ብሎ ስለፈራ አሰራቸው፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ስለኮሎኔል ዕምሩ ወንዴ ብቃት መረጃ የደረሰው ወታደራዊ መንግሥት በወቅቱ የሚጎላቸውን የአስተዳደር ክፍተት ሊሞላልን ይችላል ብለው ስላመኑ ከእስር ፈትተው የጎንደር ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው፡፡
የደርግ ፖለቲካዊ ጉዞ ያልተመቻቸው ኮሎኔል ዕምሩ በተለይም የወጣቶችን መገደል በመቃዎማቸው በአንዳንድ የደርግ ሹሞች ጥርስ ውስጥ አስገባቸው፡፡ በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ሲሄዱ የተጠሩት ሊታሰሩ መሆኑን በድብቅ መረጃ ስለደረሳቸው ወደ ገጠር በመዝለቅ የኢሕአፓን የትጥቅ ትግል ተቀላቀሉ፡፡
ኮሎኔል ዕምሩ ወንዴ በገጠር የተደራጀውን የኢሕአፓን የትጥቅ ትግል በመቀላቀል ደርግን ለመጣል ተፋልመዋል፡፡ በተለይ በጠለምት፣ በበለሳ እና በአርማርጭሆ ከነበረው የኢሕአፓ ሠራዊት ጋር በመሆን ታግለዋል፡፡ የኢሕአፓ አካሄድ እሳቸው ከሚያስቡት ጋር የሚለይ በመሆኑ ከኢሕአፓ ዓላማ ሳይጋጩ እና በኢሕአፓ የሚደገፍ “ሀገር ወዳድ” የሚባል ክንፍ አደራጅተው የደርግ መንግሥትን ለመገርሰስ ጥረዋል፡፡ በ1971 ዓ.ም “ሀገር ወዳድ” የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጠው አገልግለዋል፡፡
የጀብሃን ድርጅታዊ ህልውና እውን መሆን ያዩት ኮሎኔል እምሩ የወልቃይት ጠገዴ የትግል ታሪክ ለኢትዮጵያ የትግል መነሻ እርሾ ይሆናል ብለው ስላመኑ “የከፋኝ” ድርጅታዊ ሕልውና እውን እንዲሆን ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በዚህም ከፋኝ የኢትዮጵያ የአርበኞች ንቅናቄ በሚል ተደራጅቶ በሱዳን መንግሥትም እውቅና አግኝቶ በመንቀሳቀሱ ለኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ጥልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗል፡፡
ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ማግስት ወጣቶች ላይ በተፈጸመው ግድያ ከባድ ሐዘን ላይ የነበሩት ኮሎኔል ዕምሩ ባሉበት ኾነው የወቅቱን ትግል ይደግፉም ነበር፡፡ የከፋኝን ድርጅታዊ አቅም ለማሳደግ እና በውጭ ዓለም ያለውን አደረጃጀት ለማስፋት በአሜሪካን ሀገር የሕዝብ መድረክ ላይ በሰሜት እየተናገሩ በነበረበት ወቅት በድንገት በደረሰባቸው የመውድቅ አደጋ ለህመም ተጋለጡ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ከ45 ዓመታት የስደት ህይወት በኋላ ወደ ሚወዷት ሀገራቸው ተመልሰው በህክምና ሲረዱ ቢቆዩም ሰኔ 19/2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባላስልጣናት፤ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃወንተ ቤተክርስቲያን፣ የኮርያ ዘማቾች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ መከላከያ ማርሽ ባንድ እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብክት መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በኢትዮጵያ ጅግኖች አርበኞች መካነ መቃብር ሰኔ 24/2013 ዓ.ም ምህረት ከቀኑ 9፡00 ይፈጸማል፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ