
“አማራ ከሁሉም ወገን ጋር ፍቅር እንጂ በጉልበትና በኀይል ለመጣ ራሱን መከላከል የሚችልና በዚያ የሚታወቅ ሕዝብ መሆኑን ያስመሰከረ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር: ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተናጠል ተኩስ አቁምና መከላከያ ሠራዊቱ ትግራይ ክልልን ለቅቆ እንዲወጣ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ትናንት በምርጫ ዘገባ ለተሠማሩ ጋዜጠኞች በተዘጋጀ የምስጋና መርኃ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ውሳኔው አሸባሪው ቡድን ለሀገር አስጊ ባለመሆኑና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመኖሩ የተላለፈ እንደኾነ ገልጸዋል።
ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ቀደም ብሎ በአካባቢው የነበረውን ሠራዊትና የጦር መሣሪያ ለማውጣት የነበረው ፍላጎት በተቃውሞ መክሸፉን አስታውሰዋል፡፡ በተሠራው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ግን ሠራዊቱን እና መሣሪያውን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማውጣት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ይሕም ሌሎች ኀይሎች የሚያስቡት ነገር ካለ ለመዘጋጀት ሰፊ እድል እንደተገኘበት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡
ከሰሞኑ ሠራዊቱ መውጣቱን ተከትሎ በተሳሳተ መልኩ የሚሰራጩ አሉባልታዎች አሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ የአማራ ሕዝብ ለጥቃት እንደሚጋለጥ አስመስሎ የሚነዛውን ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ “አማራ ከሁሉም ወገን ጋር ፍቅር እንጂ በጉልበትና በኀይል ለመጣ ራሱን መከላከል የሚችልና በዚያ የሚታወቅ ሕዝብ መሆኑን ያስመሰከረ ነው” ብለዋል፡፡
“የአርማጭሆና የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ እንኳን አሁን ላለፉት 30 ዓመታት ያ ሁሉ ዱላ እየወረደበት ኢትዮጵያዊነቱንም የበጌ ምድር ሰው መኾኑንም አስመስክሯል” ነው ያሉት። በተሳሳተ መንገድ የሚሠራጩ አሉባልታዎች በተተኪ ትውልድ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መገንዘብ ማስረዳት ከጋዜጠኞች እንደሚጠበቅም አንስተዋል፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻው የታጠቀውን የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በአጭር ጊዜ አሸንፈናል፤ መልክዓ ምድሩ አስቸጋሪ ቢሆንም ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሽፍትነት የተደበቀውን ኀይል በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ማዋል ወይንም መደምሰስ ችለናል ብለዋል፡፡ አሁን ግን ሠራዊቱ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከጀርባው እየተወጋ መሆኑ አንስተዋል፡፡ በዚህም ሁኔታው በወታደሩ ዘንድ መጥፎ ስሜት ፈጥሮ በሕዝብ ላይ ጥቁር ጠባሳ እንዳይጥል፣ ሕዝቡም የጥሞና ጊዜ እንዲኖረው በማሰብ ሠራዊቱ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ሠራዊቱ ቀድሞውንም በትግራይ ክልል የመቆየት ፍላጎት እንደሌለው በማንሳትም ትኩረት የሚያሻው ሀገራዊ ጉዳይ በመኖሩ ምክንያት ገንዘባችንንም፣ ሰዎቻችንንም፣ ትጥቃችንንም ቆጥበን ወደ ዋናው ጉዳይ ብናተኩር ይሻላል በሚል ውሳኔው መተላለፉን አብራርተዋል፡፡
ደጀን ወደምንለው ሕዝብ ተጠግተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መያዝ የሚገባንን ቦታዎች ይዘን እንቆያለን፣ ወደዚያ በተደራጀ መንገድ የሚጠጋ ኀይል ካለም በደስታ ተቀብለን እናስተናግዳለን” ብለዋል፡፡
አሸባሪው ሕወኃት ሽንፈቱን አምኖ የማይቀበል መኾኑ ይታወቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠራዊቱን መውጣት ተከትሎ አሸንፌያለሁ ማለቱ ሊያስደንቅ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡ በዚህም የጠላትን የተዛባ መረጃ ማባዛት እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡
መንግሥት ባለፉት ወራት ከወታደራዊ ወጪዎች ውጭ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ለቀለብ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ትግራይ ውስጥ ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ከክልሉ አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከ14 እጥፍ በላይ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በመሠረተ ልማት ግንባታ የተሰማሩና ምግብ የሚያደርሱ ሰዎች ሲገደሉና አደጋ ሲደርስባቸው አንድም ዓለም አቀፍ ተቋምና ሰው ችግሩን ከማንሳት ይልቅ ችግሮችን በመንቀስ መንግሥትን ረፍት አልባ ለማድረግ ሲጥሩ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m