
መንግሥት ለትግራይ ክልል ያወጣው የሰብዓዊ ድጋፍ ወጭ የክልሉ የስምንት ዓመታት በጀት መሆኑን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲዔታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ናቸው፡፡
አምባሳደር ሬድዋን መንግሥት ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህም ድጋፍ የትግራይ ክልል የስምንት ዓመታት በጀት ነው ብለዋል። መንግሥት ከፍተኛ ወጭ በማውጣት የሰብዓዊ ድጋፍ እና ሌሎች ሥራዎችን ቢያከናውንም ዜጎች እንዲራቡ እያደረገ ነው በሚል ወቀሳና ሌሎች ጫናዎች መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ሀገሪቱ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ከታጣው የልማት ገንዘብ በላይ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይገኝ የነበረውን ድጋፍና ብድር እንዳታገኝ ተፅዕኖዎች ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት በትግራይ ክልል ያደረገው የተኩስ አቁም ርምጃ ሰብዓዊነት የተላበሰ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነም ተናግረዋል።
መንግሥት የተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ያስወጣው ሀገርን ለተጨማሪ የሀብት ብክነት ላለመዳረግ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች የመኸሩ ጊዜ ሳያልፍ ወደ እርሻ እንዲገቡ ያለመ ውሳኔ መንግሥት መሰጠቱንም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።
የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ የወጣው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለተደቀነባት ትልቅ የውጭ ስጋት መዘጋጀት ስላለባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ጁንታው ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር መደበኛ ጦርነት ማድረግ የቻለው ለሶስት ሳምንታት ብቻ መሆኑንም የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራሉ ቡድኑ ባለፉት ወራት ሕዝቡን በዘር በመቀስቀስ ከሠራዊቱ ጋር እንዲጋጭ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ አሸባሪው ቡድን አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ስጋት ሊሆን ከማይችልበት ደረጃ ደርሷልም ነው ያሉት።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስጋት የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በመሆኑ ለዚህ ለመዘጋጀት ጦሩ ለቆ እንዲወጣ መወሰኑን አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ