
“በኢትዮጵያ የታሪክ ሰንሰለት ውስጥ ትንናንት፣ ዛሬን እና ነገን የሚያገናኙት የጎንደር ዓለም አቀፋዊ ቅርሶች የሕልውና አደጋ
ውስጥ ናቸው” አቶ ጌታሁን ስዩም
“ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ደረጃውን የጠበቀ ሳይንሳዊ ጥገና ማድረግ ይጀመራል” ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው
ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ናት ሲባል “ድንቅነሽ”፣ ጠቢብ ነበረች ሲሏት “ላሊበላ”፣ ሕብር ነች ለሚሏት “ጀጎል”፣
ሚስጥር ናት ስትባል “የአክሱም ሐውልት” እና ታላቅ ነበረች ሲሉ ደግሞ “የጎንደር አበያተ መንግሥታት” ቀደምት ማሳያዎች
ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደርና በጉያዋ ያቀፈቻቸው ቅርሶቿ “የአፍሪካ ካሜሎት” የዚያ ወርቃማ ዘመን
ምስክሮቿ ናቸው፡፡ የ200 ዓመታት መናገሻነት አሻራ፣ የከፍታዋ ጉልላት እና የታላቅነቷ ቀስተ ደመና መቀነት ናቸው ቅርሶቿ፡፡
የቀደምት ስልጣኔዋ ማመሳከሪያ እና የታላቅነቷ ዘውዶች ናቸው የጎንደር አበያተ መንግሥታት – ለኢትዮጵያ፡፡
ከአፄ ፋሲለደስ ንግስና 300 ዓመታት ቀድማ በሕይዎት ውኃ ምንጮች እና በሰባት ተራራዎች የተከበበችው መንድር ኢትዮጵያን
ለምታክል ታላቅ ሀገር የ200 ዓመታት መናገሻ ትሆናለች ብሎ ያሰበ ባይኖርም እንኳን ልዩ የሚያደርጋትን የተፈጥሮ ውበት ያዩት
የያኔዎቹ ነዋሪዎቿ “ጎንደር” አሏት ከስም ሁሉ መርጠው ስም ሲያወጡላት፡፡
ይህች ታሪካዊ ከተማ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ፋሲለደስ እንደ ከተማ ሲቆረቁሯት ደግሞ ተፈጥሮ ብቻ ሳትሆን ታሪክም
የከተሜነት ደርዝ እና ጠርዝን አጎናጸፏት፡፡ ለ200 ዓመታት በዘለቀው መዲናነቷ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ጥበባዊ እና
መንፈሳዊ ትውፊቶቿ ጎንደርን ከኢትዮጵያ አልፈው የአፍሪካዊያን የብርሐናማው ዘመን ተምሳሌት “የአፍሪካ ካሜሎት” አደረጓት፡፡
ጠቢባን በጥበብ፣ ዜመኛ በዜማ፣ ሰዓሊ በስዕል፣ ደራሲ በድርሰት፣ ምሁራን በብዕር፣ አፍሪካዊያን በኩራት፣ ኢትዮጵያዊያን
በስስት፣ ጎብኝዎች በቅናት ስለጎንደር በፍቅሯ ወደቁ፡፡
“ጎንደር ፋሲለደስ ከግንቡ ደርሸ፤
ያለዕድል አይሆንም መጣሁ ተመልሸ” ሲሉ የተቀኙላትም ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ጎንደር ሲሉ ከአፄ ፋሲል እስከ አፄ ዮሐንስ፣
ከታላቁ አድያም ሰገድ እያሱ እስከ አፄ ዳዊት፣ ከንጉስ መሲሰገድ በካፋ እስከ እቴጌ ምንትዋብ ያሉ የጥብብ አሻራ አብያተ
መንግሥታትን አብሮ አለማንሳት አይቻልም፡፡ ጎንደር የእነዚህ ቀደምት አሻራዎች መገኛ ብቻ ሳትሆን የሚስጥራዊነቷም ቁልፍ
ናቸው፡፡
በጎንደር የሚገኙት ቤተ መዛግብት፣ የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ ቁስቋም ማሪያም፣ ራስ ግንብ እና ደረስጌ ማሪያምን አካቶ በ1970ዎቹ
ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በዓለም ቅርስነት በዩኒስኮ ተመዝግበው የዓለም ሃብት ሆኑ፡፡ ጎንደር ሌላው ሁሉ ቢቀር እንኳን እራሷን ችላ
የዓለም ቅርስ የሆነች ከተማ ነች፡፡
ዛሬ ግን እነዚህ የጎንደር ጉልላቶች የሆኑት አበያተ መንግሥታት ስማቸው የሚነሳው በአስደናቂነታቸው፣ በታሪካዊነታቸው፣
በጥባበዊ ፈጠራቸው እና በኪነ ህንፃ ውበታቸው ሳይሆን አደጋ የተጋረጠባቸው ቅርሶች ስለመሆናቸው ነው፡፡ ትውልዱን ምን
ነካው? እስኪባል ድረስ የትናንት አሻራዎቹ ላይ የሚያሳየው ቸልተኝነት አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል፡፡
የጎንደር ከተማ ዓለም አቀፍ ቅርሶች የሕልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋል እየተባለ ነውና ችግሩ ምንድን ነው? ሲል የአማራ ሚዲያ
ኮርፖሬሽን ለጎንደር ዓለም አቀፋዊ ቅርሶች አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ስዩም ጥያቄ አቅርቧል፡፡ “በኢትዮጵያ የታሪክ
ሰንሰለት ውስጥ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን የሚያገናኙት የጎንደር ዓለም አቀፋዊ ቅርሶች የሕልውና አደጋ ውስጥ ናቸው” ያሉት ዋና
አስተዳዳሪው ለችግሮቹ ዋናው ምክንያት ለቅርሶቹ ሳይንሳዊ እና በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥገና እና እንክብካቤ አለመደረጉ ነው
ይላሉ፡፡
በበርካታዎቹ አበያተ መንግሥታት ላይ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የመሰንጠቅ አደጋዎች ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ
እንደታዩ የነገሩን አቶ ጌታሁን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ካልተቻለ ችግሩ የከፋ ይሆናል ነው ያሉት፡፡ የድምፅ እና የከባድ
ተሽከርካሪዎች ብክለት፣ የሰዎች ንክኪ፣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ ከሦስተኛ ወገን ነፃ አለማድረግ እና ለቅርሶቹ እንክብካቤ በቂ
የሰው ኀይል አለመመደብ ለችግሮቹ ምንጮች ናቸው ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለቅርሶቹ ደኅንነት ሲባል ያወጣው ደንብ አፈፃፀም ውስንነት ያለበት መሆኑ ሌላኛው ችግር ነው ተብሏል፡፡ አቶ
ጌታሁን እንደሚሉት ቅርሶቹ ካላቸው ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ አንፃር ችግሮቹ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ መረባረብ
ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት እና የሚመለከታቸው ተቋማት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡
ለቅርሶቹ ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው ጥገና በርካታ ገንዘብ የሚወጣበት ነገር ግን ለዓመታት የሚዘልቅ አልነበረም ያሉን
የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ናቸው፡፡
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን 9ኙን የጎንደር አብያተ መንግሥታት የሚያካትት ጥናት እንደተጀመረ ነግረውናል፡፡ ጥናቱ ሁለት አበይት
ክፍሎችን የያዘ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የኢንጅነሪንግ ዘርፉን ኤም ኤች ኢንጅነሪንግ እና የአርክቲክቸሩን ዘርፍ ደግሞ
ፋሲል ጊዮርጊስ አርክቲክቸር እንዲይዙት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እና የሕግ ማስከበር እርምጃው ጥናቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ አድርገውት ነበር
ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ጥናቱ በከፊል ተጠናቋል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በዋናው ግንብ አካባቢ የሚገኙ ሦስት
ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ዳሰሳ እንዲደረግ የሳምንታት ጊዜ ተጨምሯል ብለዋል፡፡ ጥናቱ ተጠናቆ እንደቀረበ
ለዩኔስኮ ቀርቦና እውቅና ተፈጥሮ የጥገና ጨረታ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለ2014 የበጀት ዓመት ጥገና የሚውል 65 ሚሊዮን ብር በጀት ጠይቆ ነበር ያሉት ምክትል ዋና
ዳይሬክተሩ 35 ሚሊዮን ብር መፈቀዱን እና ከዚህም ውስጥ 25 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ለጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና
የሚውል ነው ብለዋል፡፡ በዩኒስኮ ለተመዘገቡ ሁሉም ቅርሶች የሚደረገው ጥገና በልዩ ትኩረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሠራ
መሆኑንም ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m