
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) ‹‹በመንግሥት እየታገዙ የተሳሳተ መረጃ የሚያሠራጩ እና ግጭትን የሚያባብሱ ናቸው›› በሚል ትዊተር በርካታ አድራሻዎችን (አካውንቶችን) መዝጋቱን አስታውቋል፡፡
የማኅበራ ሚዲያ ኩባንያው እንዳስታወቀው ቻይና እና ሳዑዲ ዐረቢያን ጨምሮ በስድስት ሀገራት ሀሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ እና ግጭትን ሲያባብሱ ነበሩ ያላቸውን ከ10 ሺህ በላይ አድራሻዎች ዘግቷል፡፡ ከተዘጉት መካከል ደግሞ የሳዑዲ ዐረቢያን የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ የሚያሠራጩ እና ‹‹በሆንግ ኮንግ የተፈጠረውን አመጽ ለማረጋጋት›› በሚል ሰበብ በመንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው የተሳሳተ መረጃ የሚለቁ አድራሻዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ከተዘጉት መካከል 4 ሺህ 302 በሆንግኮንግ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ የሚለቅቁ በቻይና መንግሥት ድጋፍ የተከፈቱ ሀሰተኛ አድራሻዎች እንደሚገኙበትም ታውቋል፡፡
በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው በየመን እና በሀውቲ አማጽያን የእርስ በእርስ ግጭት ላይ ያተኮረ መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ 4 ሺህ 258 አድራሻዎችም ተዘግተዋል፡፡ አድራሻዎች ከተዘጉባቸው ሀገራት መካከል ኢኳዶር፣ ግብጽ እና ስፔንም ይገኙበታል፡፡ የተዘጉት አካውንቶች በሀሰተኛ ማንነት የተከፈቱ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡
ምንጭ፡- ስካይ ኒውስ
በደጀኔ በቀለ