
“ስለ ክብር ይኖራሉ፣ ስለ ሀገር ይሞታሉ”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የታሪክ መጽሐፊያ ብዕር፣ የታላቅ ሀገር የጋራ ዜማ መዝሙር፣ የጀግንነት መነሻ፣
የኃያልነት መዳራሻ፣ የመከራ ቀን ማለፊያ፣ የማዕበል ዘመን መቅዘፊያ፣ የሁልጊዜ መኩሪያ፣ የጨለማ ቀን መውጫ መንገድ፣
የታላቅ ሕዝብ ማስተሳሰሪያ ገመድ፤ ከሰንደቅ በፊት ይዋደቃል። እናት ሀገሩን ልድፈር ወደ አለው ሳንጃ ስቦ ጦር ይሰብቃል።
መነሻው የሀገር ፍቅር፣ መዳረሻው የሀገር ክብር፣ ደልቶት አይኖርም፣ ተዝናንቶ አያድርም፣ ማደሪያው ምድር ቆፍሮ፣ ምግቡ ኮቸሮ፣
ለሕይወቱ አይሳሳም፣ ውድ ሀገሩን አያስነካም ጀግናው ወታደር።
ወታደር ታሪክ በደም የሚፃፍበት ብእር፣ ኮርተው የሚናገሩለት ዝና፣ ከዘመን ዘመን የሚዜምበት ዜማ ነው። ጀግንነት በሚበዛበት
የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደመቅ ያለው የወታደር ነው። ጦረኛ ኢትዮጵያዊ ባይኖር፣ የማያወላውል ጀግና በምድሯ ባይፈጠር ዓድዋ
ተራራ እንጂ ድል ባልሆነ ነበር። የአፍሪካ ምድር በጨለማ በኖረ ነበር። ኢትዮጵያን እንገዛለን፣ ኢትዮጵያውያንን እናስገብራለን፣
ኢትዮጵያዊነትን እናጠፋለን ያሉት ሁሉ በጀግና ልጆቿ ጠፍተዋል።
የኢትዮጵያውያን ቁጣ መብረቅ ነው፤ አድርቆ የሚጥል፣ ምትሃት ነው፤ ከሥሩ የሚነቅል፣ ረቂቅ መንፈስ ነው፤ ነብስን ከሥጋ
የሚነጥል፣ በዘመናት ቅብብል ኢትዮጵያን አጠፋለሁ ያለ የጠላት ማዕበል በወታደር ተመልሷል፣ ለኢትዮጵያውያን ይሁን የተባለ
የክፋት ፅዋ ከድንበር ማዶ ፈስሷል። የተቆለለ የጠላት ገደል ፈራርሷል። ትዕቢት የገፋው ጠላት ሁሉ የኢትዮጵያውያንን ክንድ
ቀምሷል።
ኢትዮጵያዊነት ማሸነፊያ፣ ኢትዮጵያዊነት የጨለማን ዘመን ማለፊያ፣ ኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ ኢትዮጵያዊነት ፅናት፣ ኢትዮጵያዊነት
ቀዳሚነት፣ ኢትዮጵያዊነት አይለወጤነት፣ ኢትዮጵያዊነት የድል ምልክት፣ ኢትዮጵያዊነት የመልካም ነገር ተምሳሌት ነውና።
ከኢትዮጵያዊነት ላይ ውትድርና ሲጨመርበት ደግሞ ግርማው ልዩ ነው። የዓድዋ የድል ጥላ፣ የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት መላ፣
ጠላት የማይፈታው ቀመር፣ የማይመረምረው ምስጢር፣ ኢትዮጵያዊ የማያወልቀው ዘላለማዊ ክብር ነው።
ኢትዮጵያዊያን በራስ ትጥቅና ስንቅ እየዘመቱ ማንነት እስከነ ክብሩ፣ ሀገር እስከ ድንበሩ አቆይተዋል። የቀደሙት ኢትዮጵያውያን
ሲያልፉም የማይሻር፣ የማይረሳ ቃል ኪዳን አደራ ብለዋል፣ ልጆቻቸውን በቃል ኪዳን አስረዋል። ቃል ኪዳን ያሰራቸው፣ የአባቶቻቸው
የጀግንነት ታሪክ ያላስተኛቸው፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የዋጃቸው፣ የሀገር ክብር የጠራቸው ጀግና ልጆች ዛሬም እንደ ትናንቱ
“እማማ ሆይ አለንልሽ፣ እኛ እያለን ክብርሽም ስምሽም ዝቅ አይልም” እያሉ ነው።
“አልማከርም ከፈሪ ጋራ፣
ያስደፍረኛል ወሬ ሲያወራ” የሚሉት ጀግኖቹ ምክራቸው ከጀግና ጋር ውሏቸው ከሀገር ድንበር ነው።
ድሎት ሳያምራቸው፣ የወገን ናፍቆት ወደኋላ ሳይጎትታቸው፣ መከራ ሳያደክማቸው፣ ቁሩና ሀሩሩ ሳይበግራቸው፣ ለእማማ ኢትዮጵያ
ምቾትንና ሕይወትን ሰጥተው ይኖራሉ። ስለ እርሷ ሲሉ ይኖራሉ፣ ስለ እርሷም ያልፋሉ። በስሟ ምለው፣ ለቃሏ ታምነው፣ ለክብር
ብለው መሪር ፅዋን ይቀምሳሉ፣ ክፉ ቀንን ይታገሳሉ።
“እኔ ላገሬ አደራ አለብኝ፣
ጎጆ ትዳሩም ከዚያው ይቅርብኝ፣
ሀገሬን ጠላት ከሚደፍርብኝ፣
ድንበር ዘምቸ ከሠንደቋ ሥር መሞት አለብኝ” እንዳለ አርበኛው ሁሉም ነገር ይቅርብኝ ብለው ለሀገር ማገር፣ ለወገን ክብር ሊሆኑ
ፅኑ ቃል ኪዳን ያስራሉ።
አዳሬ ማርና ወተት፣ ጮማና እሸት፣ ጠጅና ጠላ ከሚገኝበት ደግነት እንደ ዥረት ከሚፈስበት፣ ጤፍ እንደ አሸዋ ከሚታፈስበት
ፍኖተ ሰላም ዳሞት ጎጃም ነው። ጎጃም ደግነትና ጀግንነት እንደ ግዮን ምንጭ ይፈስሳል። በመልካሙ ምድር ክረምት ከበጋ
ይታረሳል፣ ጤፍና፣ ዳጉሳ፣ ስንዴና በቆሎ እንደ አሻ ይታፈሳል። ጎተራው ሲሞላ፣ ሀገር ሲሆን ደህና ደግሞ በእንቅጥቅጥ ጭፈራ፣
በባሶ ዳንኪራ፣ በጎጃም ድለቃ ዓለም ይታያል።
ጨለማ ካባውን ሲገፍ፣ ምድር በብርሃን ስትጎናፀፍ ከእንቅልፌ ነቃሁ።
“እንደምነው ጎጃም ዳሞት ብርሸለቆ፣
ጭንቅ ያለ ጊዜ የሚደርሰው ታጥቆ” እንደተባለው ከወደ ብርሸለቆ የታጠቁ፣ የበቁ ጀግኖችን አይ ዘንድ እድል ገጥሞኛልና ለጉዞ
ተዘጋጀሁ። በሰላም ያረፍንብሽ ሰላም ይረፍብሽ፣ እንደ ስምሽ የሰላም ማረፊያ ፍኖተ ሰላም ሆይ ደህና ሁኚ አልኳት።
ፊታችን በሐዲስ ዓለማየሁ ብእር በጥበብ ወደ ሰፈረችው፣ በየሰው ልብ ውስጥ ተቀርፃ ወደ ተቀመጠችው፣ ማንኩሳ ከተማ
አዙረን ጉዞ ጀመርን። ማንኩሳ በታላቁ የጥበብ ሰው የሰፈረች፣ በልብ ውስጥ የታታመች፣ እንደ ስሟ ግዝፈት ያልዘመነች አሳዛኝ
ከተማ። በፍቅር እስከ መቃብር ማጀቢያ ዜማ በእዝነ ልቦናችን፣ ወገግ ባለ ማለዳ በዓይናችን ቃኝተናት ወደ ብርሸለቆ
የሚወስደውን መንገድ ይዘን ቀጠልን። ከከተማዋ ወጣ ብለው ጥቂት እንደተጓዙ በመንገዱ በግራና በቀኝ፣ ለዓይን ማረፊያ
የተመቻቸ ቡቃያ ይመለከታሉ። ለምለሙ ምድር አረንጓዴ ካባውን እያጠለቀ ነው። ለዓይን ምግብ፣ ለነብስ ሀሴት በሚሰጠው
መልካም ማሳ መካከል በተሠራው የጠጠር መንገድ እየተጓዝን ዓይኔ ባሻገር ይቃኛል። ምድሩ ተውቧል። ሀገሩ አምሮበታል።
ከፊት ለፊታችን በዛፍ ሥር ለሥር የተመሰረተች ትንሽዬ መንደር አገኘን። ስሟም ላይበር ትሰኛለች። ቃኝተናት ዓለፍን። ከመዳረሻን
ለመድረስ ተቻኩለናል። ጉዟችን ቀጠለ።
በአሻገር አረንጓዴ ካባ የተጎናጸፈ መልካም ተራራ ይታዬን ጀመር። ከተራራው ግርጌ ደግሞ በእኩልነት እደጉ የተባሉ በሚመስሉ
እፅዋት የተዋበ ውብ ምድር ይታያል። የልባችን ጉጉት ጨምሯል። የማዬት ፍላጎታችን አይሏል። ወደፊት ገሰገስን፣ በአረንጓዴ
እፅዋት በተዋበው ምድር በተሠራች የጠጠር መንገድ ፊት ለፊት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቁን ከፍ ብሎ ተመለከትን። የልቤ ሀሴት
ሲታገለኝ ተሰማኝ። ወደፊት ተጠጋን።
ብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚል ጽሑፍ ተመለከትኩ። ልቤ ከሻተው ደርሷልና ደስ አለኝ።
ከማስልጠኛ ትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ወኔ የሚሰጡ ቆፍጣና ወታደሮች ቆመዋል። መልካም አቀባበል አደረጉልን። ወደ ውስጥ
እንዘልቅ ዘንድም ጋበዙን። ወደ ውስጥ ሲገቡ ከበሩ ላይ “ለሀገራችን ሉዓላዊነትና ለሕዝባችን ሰላም ዘብ እንቆማለን፣
በሠለጠንኩት ወታደራዊ ሙያ ሀገርና ሕዝብን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ” የሚል ጹሑፍ ይመለከታሉ። አዎን በዚያ አስፈሪ ቦታ
ውስጥ ያልተዘጋጀ ሰው የለም። ሁሉም ዝግጁ ነው።
ውሎዬ ብርሸለቆ ነበር። ዙሪያ ገባው ያስፈራል። በአረንጓዴ ደን የተሸፈነው አካባቢ ልብ ይፈታተናል። በዚያ ውስጥ አንበሳና ነበር
ይኖር ይሆናል እንጂ ማን የሰው ልጅ ይኖርበታል ብሎ ያስባል። የዱር እንስሳት መናኸሪያ፣ የአእዋፋት መዘመሪያ ሥፍራ
ሊመስለዎትም ይችላል። ዳሩ ይህ አይደለም በዚያ ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ አንበሳ ወታደር ነው። ዓይኔ ከሚያየው አዳዲስ
ነገር መብዛት የተነሳ ከየትኛው ላይ ማረፍ እንዳለበት ለመምረጥ ተቸግሯል። አንዴ ከዛፉ፣ አንድ ጊዜ ከታጠቁ ወታደሮች፣ ሌላ
ጊዜ ደግሞ ከማሰልጠኛ መሳሪያዎች ላይ እያማተረ ይንከራተታል።
አጄብ ነው። በዚያ አሰፈሪ ሥፍራ ውስጥ እናት ሀገራቸውን ለመጠበቅ የተዘጋጁ ውድ ልጆች አሉና መርቁ ተብለው የተጠሩ
ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች በአፀደ ግቢው ውስጥ ተገኝተዋል። ለሚመርቋቸው ጄኔራሎች ትርኢት የሚያሳዩ ተመራቂዎች ደግሞ
በተጠንቀቅ ቆመዋል። ጄኔራሎቹ በለምለሙ ግቢ ውስጥ ተጨማሪ ውበት ይሆን ዘንድ ችግኝ ተክለው ወደ ሚመርቋቸው
ወታደሮች አቀኑ። እኔም ተከተልኳቸው። የወታደሮቹ ፍጥነት፣ ጥንካሬ፣ ወኔና የአሸናፊነት ስሜት ግሩም ነው። ከቀላል እስከ
ውስብስብ የወሰዷቸውን ስልጠናዎች በሚገባ አሳዩ። ታዳሚ እንግዶችም በደስታና በግርምት አጨበጨቡላቸው። እኔ ግን
ትርኢት ሳይሆን የምር ጦር ሲመስለኝ ነበርና፣ አግራሞትም ድንጋጤም ይሰማኝ ነበር።
ኢትዮጵያ ሆይ መታደልሽ፣ ከቀደሙት ቀደምሽ፣ ከዘመናት በፊት ዘመንሽ፣ ሳትደፈሪ ተጠበቅሽ፣ ሳትሰስቺ ጀግና ወልድሽ፣ ከዘመን
ዘመን ኮራሽ፣ በውድ ልጆችሽ ታፈርሽ ተከበርሽ፣ አንቺስ ተመርጠሻል። አንቺን የሚመስሉ በዓለም ላይ የሉም። አንቺ ለሌሎች
መሪያቸው፣ ጨለማውን አሻጋሪያቸው፣ ከፍ ያልሽ ምልክታቸው ነሽና ደስ ይበልሽ አልኩ በልቤ። ኢትዮጵያ እያለ ደጋግሞ
የሚጠራትን ወታደር ሳይ ልቤ በሀሴት ተመላች። የተኩሱና የስፖርቱ ትርኢት የወታደሮቹ ፍጥነት ግሩም ድንቅ ብሎ ዝም ከማለት
ውጪ ምን ይባላል?
የትርኢቱ ጊዜ ተጠናቋል። ሀገራቸውን ለማገልገል፣ ቃል ኪዳናቸውን ለማሰር፣ ሠንደቃቸው ከቀደሟቸው ጀግኖች ለመቀበል
የተዘጋጁ ወታደሮች ወደ ተሰበሰቡት ሜዳ አቀናን። ውበታቸው፣ ወኔያቸው፣ ግርማቸው፣ ኢትዮጵያ የሚለው የጋራ ዜማቸው፣
በአንድ ላይ ያስተሳሰራቸው ኢትዮጵያዊነታቸው በደስታ ያቀልጣል። በመገረም ውቅያኖስ ውስጥ ያሰምጣል። ከተጨናነቀ ሐሳብ
ያስመልጣል። በሥርዓት በተሠደሩበት ሜዳ ውስጥ እንዳሻኝ ተመለከትኳቸው። ልቤ በደስታ ጠገበች፣ አብዝታም ተገረመች።
ኢትዮጵያ ታድለሽ፣ ቃልሽን የሚያከብር፣ ታሪክሽን የሚዘክር፣ ድንበርሽን የሚጠብቅ ልጅ በአዲስ ኃይል መጥቶልሻልና ኩሪ ለኩራት
የተፈጠርሽ አልኩ።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ሊወዳት ይችላል፣ እንደ ወታደር ግን የሚወዳት ያለ አይመስለኝም። ሌላው ስለ ፍቅር ጉልበቱን፣
እውቀቱን ግፋ ቢል ሀብቱን ሊሰጣት ይችላል። ወታደር ግን ስለ ፍቅርና ስለ ሀገር ክብር ከምንም በላይ የሆነውን ሕይወቱን
ይሰጣል።
እኒያ ጀግኖች በጎዳና ሲያልፉ ሕዝቡ ሁሉ ከመቀመጫው ተነስቶ ቢያጨበጭብላቸው፣ በአሻገር ሲታዩ እጅ ቢነሳላቸው፣ ባገኛቸው
አጋጣሚ ሁሉ ፍቅርና ክብር ቢሰጣቸው ያንስባቸው እንደሆነ እንጂ አይበዛባቸውም። እነርሱን ከማድነቅ ውጭ ምን ሊባል
ይችላል?
ራሴን ታዘብኩት፣ ሀፍረት ተሰማኝ። በስስት አየኋቸው፣ ልቤን በፍቅር ወሰዷት። እናንተ ጀግኖች ተመርጣችኋል፣ ታድላችኋል፣
ተከብራችኋል፣ ታላቁን ሙያ ይዛችኋል፣ ታላቁን ቃል ኪዳን አስራችኋል፣ ፅኑውን መንገድ ጀምራችኋል አልኩ በልቤ።
ሕግ አክባሪነት፣ ታዛዥነት፣ ትዕግሥት፣ ፅናት፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ጀግንነት፣ ቃልን ጠባቂነት፣ አርቆ አሳቢነት የጋራ
ዜማቸው፣ የጋራ የክብር ልብሳቸው፣ የጋራ ማዕረጋቸው፣ የጋራ ሽልማታቸው ነው። በዚያ ግቢ ውስጥ ታናሽ ታላቅን አክባሪነት፣
ታላቅ ታናሽን ወዳጅነት፣ ተመሪ አዛዥን ሰሚነት፣ መሪ ተመሪን በጥበብ ያዥነት ይማራሉ።
የጠፋ የመሰለን እሴት፣ የተሸረሸረ የመሰለን አክብሮት በዚያ ግቢ ውስጥ ከፍ እንዳለ አለ። ወታደሮቹ በዚያ አስፈሪ ሥፍራ
ቃላቸውን አሰሩ፣ ሠንደቃቸውን ተቀበሉ፣ መለዮዓቸውን ለበሱ፣ ለግዳጅ ዝግጅታቸውን ጨረሱ። የእናት ሀገር ድንበር፣ የወገን
ክብር እንዲጠበቅ ጉልበት ሳይሆን ሕይወት ለመስጠት ማሉ። እነርሱ ስለ ክብር ይኖራሉ፣ ስለ ሀገር ይሞታሉ። በብርሸለቆ በረሃ
ውስጥ በሕብረት በቆሙት ወታደሮች ፊት ውስጥ ኢትዮጵያን አየኋት፣ ለክብር ተዘጋጅታለች፣ ከፍ ለማለት ቆርጣ ተነስታለች።
ለልጆቿ አደራዋን ሰጥታለች። በልጆቿም ትተማመናለች። አቤቱ እኒያን መሰል ልጆች አብዛቸው፣ ለክብር ነውና የቆሙት
አክብራቸው። ለሰላም ነውና የቆሙት ከፊት ቅደምላቸው። ዝግጅቱ ተጠናቋል፣ የእኔ መገረም ግን እንደቀጠለ ነው። ልቤ
ከብርሸለቆ በረሃ፣ ከአስፈሪው ሰማይ ሥር፣ ከዛፎቹ ግርጌ፣ ከወታደሮቹ አጠገብ እንደቆመ ነው።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m