
“የአማራ ሕዝብ በሽብርተኞች ሂሳብ እንዲወራረድበት አይፈቅድም” የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች በተደጋጋሚ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት የአማራን “ኢሊት” ተጠያቂ በማድረግ ሂሳብ
እንደሚያወራርዱ ነግረውናል። ትህነጎች የሚያወራርዱትን ሂሳብ “ከአማራ ልሂቃን” ጋር ያያይዙት እንጂ እውነታው ግን የአማራን
ሕዝብ ስለማለታቸው ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለንም። ለዚህ ተጨባጭ ግምገማ አስረጅ ምሳሌው ትህነግ በታሪካዊ ጠላትነት
የፈረጀው የአማራን ሕዝብ እንደአጠቃላይ እንጂ የአማራን ልሂቃን በለዬ ሁኔታ አይደለም። ስለሆነም የትህነጎች ሂሳብ ማወራረጃ
የአማራ ሕዝብ እንጂ ልሂቁ ብቻ አይደለም። ይህ አዲሱ ማደናገሪያቸው ነው። ጥላቻቸው በአማራ ሕዝብ ላይ ነው። ስሁት ትርክት
የፈጠሩት፣ ለዚህ ማስፈጸሚያ መዋቅር የነበሩት ልሂቁን ብቻ ሳይሆን አማራን እንደሕዝብ ለመጉዳት ሆነ ብለው አስበው፣
አቅደውና አጥንተው ነው። ጥላቻው የአማራ አርሶ አደር ጓዳ ድረስ የዘለቀ ነው።
በተግባር ፈጽሞ የማይሳካ ቢሆንም በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ዛሬ “ሂሳብ እናወራርዳለን” ሲሉ ቢሳካላቸው የአማራ አርሶ አደር ጓዳ ድረስ
የዘለቀ የሰይፍ በትር የመዘርጋት ሰይጣናዊ ተነሳሽነት አላቸው።
በትህነግ የሂሳብ ማወራረድ እሳቤ የሚዘረፈው ንብረት የአማራ ሕዝብ ንብረት ሲሆን፤ ሊደፈሩ የታሰበው ደግሞ የአማራ እናትና
እህት ናቸው። ተገዳዩ ደግሞ ሁሉም አማራ ነው።
ይሁንና ዛሬ መላው የአማራ ሕዝብ በትህነግ ዳግም ሊሰነዘርበት የታሰበውን የጥፋት ሰይፍ በደንብ ተረድቶታል። የብሔራዊ ንቃት
ስሜቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል። የሞራል ልዕልና ከፍታውን ባለበት አስጠብቋል። በፍቅር ለመጣ በተለመደ ሰብዓዊ
ጀግንነቱ እጁን ይዘረጋል፤ በጥላቻ ለሚመጣ ተገቢውንና የማያዳግም ትምህርት ሰጥቶ ይመልሳል።
የአማራ ሕዝብ የትኛውንም በቀል ለመበቀል ፍፁም አልተዘጋጀም። ይህ ማለት ግን “ሂሳብ እናወራርዳለን” ባዮችን በዝምታ
ይታገሳል ማለት አይደለም። ከዳተኛና ጸረ-ሕዝብ የሆኑ የትኞቹንም ጠላቶቹን ያለ ምህረት ይታገላል።
ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ
እናሳውቃችኋለን።
እነዚህን አካባቢዎች ደግሞ ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ፣ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌለ
መሆኑን ደግመን ደጋግመን እናረጋግጥላችኋለን።