
“የአረንጓዴ ልማትን በማጠናከርና ችግኞችን በመትከል ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ማድረግ ይገባል” ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
ባሕር ዳር: ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በማጠናከርና ችግኞችን በመትከል ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ማድረግ እንደሚገባ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በለገዳዲ ተፋሰስ አካባቢ የችግኝ ተከላ መርኃግብር ዛሬ አካሂዷል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚኒስቴሩና ከተጠሪ ተቋማት ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በማጠናከርና ችግኞችን በመትከል ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ እንዲሁም ለጎረቤት ሀገራት ደግሞ 1 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል። ዝግጅቱ እንዲሳካ ሚኒስቴሩ ከግብርና ሚኒስቴርና ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ሕዝቡ በስፋት በመሳተፍ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ የዓባይ ተፋሰስን ለማልማት በየዓመቱ ችግኞችን የማልማት ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተያዘው የክረምት ወራትም በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ የሚተከሉ 74 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው የውኃ መሠረተ ልማቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ባለፈው ዓመት ከተተከሉት 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኞች 1 ነጥብ 6 ቢሊየኑ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ መተከላቸውን አስረድተዋል።
በዘንድሮ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል ከታቀደው ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ እንደሚተከል አብራርተዋል።
በዛሬው የችግኝ ተከላ መርኃግብር ላይ የተሳተፉት አቶ ጎሳዬ ደምሴ፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማድረግ ኹላችንም የድርሻችንን መወጣት አለበን ነው ያሉት።
በመርኃግብሩ ላይ በስምንት ሄክታር መሬት 10 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል፤ የሎሚና አፕል የፍራፍሬ ችግኞችም ተካተውበታል። ኢዜአ እንደዘገበው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ