ኢትዮጵያ እኤአ በ2017 ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት እየሠራች መሆኑ ተገለጸ።

378
ኢትዮጵያ እኤአ በ2017 ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት እየሠራች መሆኑ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ለመቅረፍ ያለመ ውይይት በባሕር ዳር ተካሂዷል።
ውይይቱን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ናቸው። በኢትዮጵያም ኾነ በአማራ ክልል ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ችግር ኾነው መቀጠላቸው ውይይት ተደርጎበታል።
የሰሜን ምዕራብ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የቦርድ አባል በልአንተ አክሊሉ የሴት ልጅ ግርዛት ጎጂ መኾኑን በቤተ እምነታቸውም ኾነ ሳይንሳዊ እውነታን በማመሳከር እያስተማሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ያለእድሜ ጋብቻም ኾነ የሴት ልጅ ግርዛት ተገቢ አለመሆኑን በተመለከተ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
መልአከኀይል አዕምሮ ዋካ የሰሜን ጎንደር ደባርቅ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ናቸው። ያለእድሜ ጋብቻ በተለይ ሁለቱ አካላት ካልተስማሙ በስተቀር በሌላ ወገን ተጽዕኖ ጋብቻን መመስረት በሃይማኖታቸው የተከለከለ መኾኑን አስረድተዋል። የውይይቱ ተካፋይ መኾናቸው ደግሞ ይበልጥ ልጆች እድሜያቸው ለጋብቻ ሲደርሱ ብቻ ጋብቻ እንዲፈጽሙና በትዳራቸው እንዲጸኑ ትምህርት ለመስጠት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል። “ጋብቻ መስራቾች ከጋብቻ በፊት በአስተሳሰብና በአካል ጠንካራ መኾን አለባቸው” ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን እስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሻምበል ሙስጠፋ ሙሉዓለም ሴትም ኾነች ወንድ ያለእድሜያቸው እንዳያገቡ ቅዱስ ቁርአን ይከለክላል ብለዋል። በአካባቢያቸው በርካታ ያለእድሜ ጋብቻን እንዲሰረዙ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ሴት ልጅ አካሏና አዕምሮዋ ለትዳር ብቁ ካልሆነ ቤቷንም በትክክል መምራት አትችልም ነው ያሉት።
የሴት ልጅ ግርዛት በተለይ ያለእድሜ ጋብቻ በአማራ ክልል ያለበትን ሁኔታ፣ እያስከተለ ያለውን ችግርና መፍትሔ የሚጠቁም የውይይት መነሻ ጽሑፍም በመድረኩ ቀርቧል። የመነሻ ጽሑፉን ያቀረቡት በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ስማቸው ዳኜ ናቸው።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2018 ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባወጣው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ የሕፃናት ጋብቻ በከፍተኛ ደረጃ ከሚስተዋልባቸው 50 ወረዳዎች ውስጥ 23 ወረዳዎች በአማራ ክልል ይገኛሉ ብለዋል። በአማራ ክልል በ2013 ዓ.ም በተሰበሰበው መረጃ መሠረት በ2012 ዓ.ም 5 ሺህ 763 ሕፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ ኾነው የተዳሩ ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ 4 ሺህ 19 ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ አቶ ስማቸው ባቀረቡት ጽሑፍ አመላክተዋል።
የቆየ ወግና ሥርዓት፣ ብድር ለማስመለስ፣ ዝምድና ለመመስረት ዋነኛ ያለእድሜ ጋብቻ መመስረቻ መንስኤዎች መኾናቸውን አቶ ስማቸው አስረድተዋል። “ኅብረተሰቡ ያለእድሜ ጋብቻም ኾነ የሴት ልጅ ግርዛትን መፈጸም እንደሚያስጠይቅ በቂ ግንዛቤ አለው” ያሉት አቶ ስማቸው የኅብረተሰቡ ችግር ድርጊቶቹ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አለመረዳቱ ነው ብለዋል።
ያለእድሜ ጋብቻ ፊስቱላን ጨምሮ ሌሎች አካላዊ ጉዳቶችን ከማስከተሉ ባሻገር ለፍቺ፣ ለፍልሰት፣ ለሴተኛ አዳሪነት፣ ለመገለልና ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶችን እንደሚያስከትል አቶ ስማቸው ባቀረቡት ጽሑፍ አረጋግጠዋል።
በመኾኑም በተለይ የሃይማኖት አባቶች ድርጊቱን መከላከል የዘወትር ሥራቸው መኾን አለበት ብለዋል። ኅብረተሰቡም የሚያስከትለውን ጉዳት ተገንዝቦ እነዚኽን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስቀረት ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
የተቀናጀ ሥራን በመሥራት፣ ከአሁን በፊት ድርጊቶቹን ለመግታት የተሠሩ ሥራዎችን በ 8 እጥፍ በማሳደግ ኢትዮጵያ በ2017 ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት እየሠራች መኾኑን አመላክተዋል። ይኽን ለማሳካትም የኹሉንም ወገን ቁርጠኛነት ይጠይቃል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር በተፈጠረው ችግር ከቀያቸው ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ።
Next article“የአረንጓዴ ልማትን በማጠናከርና ችግኞችን በመትከል ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ማድረግ ይገባል” ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ