ተመራቂ ወታደሮች በፍፁም ወታደራዊ ሥነ ምግባር ግዳጃቸውን እንዲወጡ ሜጄር ጄኔራል ሐጫሉ ሸለመ አሳሰቡ።

283
ተመራቂ ወታደሮች በፍፁም ወታደራዊ ሥነ ምግባር ግዳጃቸውን እንዲወጡ ሜጄር ጄኔራል ሐጫሉ ሸለመ አሳሰቡ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት በብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት ዘርፍ ዋና ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ሐጫሉ ሸለመ፣ የምድር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ምክትል አዛዥ ለሰው ሃብት ልማት ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደ ኪዳን፣ መከላከያ ሠራዊት የሴቶች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌን ጨምሮ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል።
ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮቹ በማሰልጠኛ ተቋሙ ያገኙት የንድፈ ሐሳብና የተግባር ስልጠና በግዳጅ ጊዜም እንደሚፈፅሙ ተናግረዋል። ሀገርና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ በቁርጠኝነት ለመፈፀም ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል። ተከብራ የኖረችን ሀገር ለማስከበርና ክብሯን ለማስቀጠል በፍፁም ኃላፊነት ግዳጅ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ዋና አዛዥ ኮሎኔል ጌታቸው አሊ ክቡር የሆነውን የውትድርና ሙያን መርጣችሁ ለዚህ ደግና ጀግና ሕዝብ የሕይወት ዋጋ ለመክፈል፣ ውድ ሀገራችሁን ለማገልገል ወስናችሁ፣ አፍራሽ ጥላቻና የጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይበገራችሁ ለምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋቸዋል።
የብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የተቀመጠውን መመልመያ መስፈርት የሚያሟሉ ኢትዮጵያውንን ተቀብሎ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የተመሠረተ ስልጠና በመስጠት ወታደሮችን እንደሚያፈራ ነው የገለፁት። ማሰልጠኛ ተቋሙ ለ33ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ወታደሮች ማስመረቁንም ተናግረዋል ።
ማስልጠኛ ተቋሙ በሀገር መከላከያ የተሠጠውን ሀገራዊ ተልእኮ እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ሰልጣኞቹ በሥርዓተ ትምህርቱ የተቀመጠላቸውን ትምህርቶች መውሰዳቸውንና የሠራዊቱን ተልእኮ በሚገባ መማራቸውን ነው የተናገሩት። ተመራቂዎቹ በማሰልጠኛ ተቋሙ እውቀትና ብቃት ማስመዝገባቸውንም ተናግረዋል። ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገለግል ብቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ውትድትና የተከበረ ሙያ ነው ያሉት ዋና አዛዡ ራስን ለሕዝብ አሳልፎ በመስጠት ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ መቆም ነውም ብለዋል። የተቋሙን እሴቶች በመላበስ በስልጠና ያዳበሩትን ብቃት በተግባር ላይ በማዋል በታማኝነትና በታታሪነት እንደሚያገለግሉም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት ዘርፍ ዋና ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ሐጫሉ ሸለመ “በራሳችሁ ፍላጎት ለዜግነት ተጋድሎ ወታደር በመሆናቸሁ ኢትዮጵያ ሀገራችሁ ትኮራባችኋለች” ብለዋል ተመራቂዎቹን።
ከኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመምጣት በአንድ ላይ በመሰባሰብ ኢትዮጵያ ምን ያክል ታላቅ ሀገር መሆኗን አሳይታችኋልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያን በመምረጥ ዓለምን ባስደመሙበት ማግሥት መመረቃችሁ ልዩ አድርጓችኋልም ነው ያሏቸው።
ጦርነት አክሳሪና አውዳሚ በመሆኑ ጦርነት እንዳይኖር የሰላም ዘብ በመሆን ጦርነትን ለማስቀረት አቅምን በማሳደግና ጠንካራ የሀገር መከታ ለመሆን መዘጋጄት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። በመከላከያ ውስጥ ጥራትና ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲኖርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲቻል እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
“የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሆነን መለዬ ለብሰን ቃል ስንገባ የሀገር ሰንደቅ ዓላማና የሕዝብ አደራ እየተቀበልን መሆኑን አውቀን ለስመ ገናናዋ የሀገራችን ክብር እንዲሁም የሕዝብ አደራ ለመጠበቅ በወታደራዊ ስነምግባር ታንፀን፣ እሴቶቻችንን ተላብሰን፣ በማንኛውም ሁኔታ በሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስና የሕዝባዊ ወገንተኝነትን ጠብቀን ግዳጅ መፈፀም ይጠበቅብናል” ነው ያሉት።
ከሕዝብና ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን በማስቀደም የሚሠሩ ኃይሎች ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖር እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ከውጭና ከውስጥ የተደራጁ ኃይሎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት የምንከታተልበትና ጥቃቶችን ለመመከት የምንሰማራበት ወቅት ነውም ብለዋል። በፍፁም ወታደራዊ ሥነ ምግባር ግዳጅ እንዲወጡም አሳስበዋል ሜጄር ጄኔራሉ።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ – ከብርሸለቆ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ከትምሕርት ውጪ የሚባክን ጊዜ አልነበረኝም” 4 ነጥብ ያስመዘገበው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ
Next articleየትራንስፖርት ሚኒስቴር ክረምቱን በሚካሄደው የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ላይ በአጋርነት እየተሳተፈ መሆኑን ገለጸ፡፡