
“ከትምሕርት ውጪ የሚባክን ጊዜ አልነበረኝም” 4 ነጥብ ያስመዘገበው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ከ 3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በ9 የትምህርት ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው፡፡ በመርኃ ግብሩ በትምሕርታቸው ስኬታማ የነበሩ ተመራቂዎች የነበራቸውን ቆይታ አስታውሰዋል፤ የተሰማቸውንም ደስታም ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ከአግሮ ኢኮኖሚክስ ትምሕርት ክፍል 4 ነጥብ በማምጣት የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚው ጌታቸው ዓለሙ የሦስት ዓመታቱ የትምሕርት ጊዜ ፈታኝ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ በግል ብርቱ ትጋት፣ ከትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች ጋር በመረዳዳት፣ የትምሕርት ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም በመምሕራንና በቤተሰብ ድጋፍ ውጤታማነቱን አስጠብቆ እንዲያጠናቀቅ አድርጎታል፡፡
ያጋጠሙ ፈተናዎችንም በድል ተወጥቷል፡፡ “በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ከትምሕርት ውጪ የሚባክን ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ሦስቱንም ዓመታት ጊዜዬን ሳልሸራርፍ ተምሬያለው፣ ለውጤትም በቅቻለሁ” ብሏል ተማሪ ጌታቸው፡፡ በተለይ ሳይማሩ ያስተማሩት ቤተሰቦቹ ድጋፍ በትምህርቱ ውጤታማ እንዳደረገው አንስቷል፡፡
የተመራቂው አባት ቀሲስ ዓለማየሁ ልጃቸው ገና ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ አንደኛ ደረጃን እየያዘ ማጠናቀቁን አንስተዋል፡፡ በተለይ ከፍተኛ ሕመም ቢጋጥመውም ከትምሕርቱም ኾነ ከውጤታማነቱ እንዳላገደው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ