“ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ችግር አልፋ ወደ ተሟላ ብልፅግና እንድትደርስ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከቱ የተሟላ ሰው ያስፈልጋታል” የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር)

264
“ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ችግር አልፋ ወደ ተሟላ ብልፅግና እንድትደርስ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከቱ የተሟላ ሰው ያስፈልጋታል” የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡ በዚህ ወቅት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር) በዓለም አቀፍ ወረርሽኝና በተለያዩ ችግሮች አልፈው ዛሬ የተመረቁ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቁጥር ከፍያሉ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት በማስተማር ላይ መኾኗንም አብራርተዋል፡፡ ሀገሪቱ አሁን ከአለችበት ችግር እንድትወጣም ተመራቂ ተማሪዎች ትልቅ አቅም መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ለትምህርትና ስልጠና ገንዘብ በመመደብ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማሰልጠን ወደ ሥራው ዓለም እያስገባ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ያለው ችግር የትምህርት ማነስ ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ኢትዮጵያን አሻግሮ የሚመለከትና የዛሬን ፈተና በነገ ስኬት የሚመዝን ትውልድ ለመፍጠር ትምህርት ትክክለኛው መንገድ ነው ብለዋል፡፡
ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ የዕድሜ ልክ ተማሪ ለመኾን መዘጋጀት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ “ከነገዋ ቀን ጀምራችሁ በዕየለቱ ከታላላቅ ሰዎችና ከኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እንድትማሩ አሁንም አደራ እንላለን” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ችግር አልፋ ወደ ተሟላ ብልፅግና እንድትደርስ በእውቀት በክህሎትና በአመለካከቱ የተሟላ ሰው ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ የሰባዊ ልማቱ ትኩረትም ይህንን ማሳካት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “የተማረ ሰው ሳይኖር የተስተካከለ ሀገር መገንባት አይቻልም” ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፡፡ በዕውቀት የበለጸገ ሰው ሳይኖር ኢኮኖሚን በፍትሐዊነት ማሳደግና መጠቀም እንደማይቻልም አስገንዝበዋል፡፡ ይህንን የተረዱ ዩኒቨርሲቲዎችም የተሟላ ስብዕና ያለውን ዜጋ ለመገንባት በተደራጀ አግባብ ሥራቸውን እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡
“ደብር ብርሃን ዩኒቨርሲቲም አፕላይድ ተብሎ ሲሰየም በቅርብ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት በመሥራት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ዕድገት እንዲወስድ ታሳቢ በማድረግ ነው፤ ሥራውንም በአግባቡ እየተወጣ ነው” ብለዋል፡፡
ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ለመምህራን ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎችም በቀጣይ የሚገጥማቸውን ፈተና ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጁ መኾን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በአዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleከፈረንሳይና ከጣሊያን መንግሥታት ጋር የተደረጉ የመከላከያ ስምምነቶች ጸደቁ፡፡
Next article“ከትምሕርት ውጪ የሚባክን ጊዜ አልነበረኝም” 4 ነጥብ ያስመዘገበው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ