አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ለምን …?

776

ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊና ዕድሜ ጠገብ ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው፤ ገዳሙ ከደሴ በ180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የታሪክና የቅርስ አምባ መሆኑም ይነገርለታል፡፡ በ12ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተም ታሪኩ ያስረዳል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፡፡

ገዳሙ ቀደም ብሎ የተመሠረተ ቢሆንም የበለጠ ዕውቅና አግኝቶ የተገደመው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተባሉት ደራሲ መምህር ሐዋርያ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሥነ ምሕንድስና አዋቂና ኪነ ጠበብት መሆናቸውን ገድላቸው ያስረዳል፡፡

ገዳሙ ከደብረ ዳሞ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከመሬት ወደ ላይ 47 ሜትር ርቀት አለው፡፡ የሚወጣውም በእንጨት በተሠራ መሰላል ነው፡፡ ወደ ገዳሙ መውጫም ሆነ መግቢያው ይኸው ጥንታዊ መሰላል ነው፡፡ ስምንት ፍልፍል በሮች፣ ስምንት ጥርብ ምሰሶዎች፣ አምስት የቅዳሴ ሥርዓት የሚፈፀምባቸው ክፍሎች ያሉት የዋሻ ውስጥ ገዳም ነው፡፡

በ16ተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አህመድ ጦር በደረሰበት ጉዳት ተዘግቶ የቆየ አሁን ‹የአቦ ዋሻ› እየተባለ የሚጠራ ፍልፍል ዋሻ የያዘና የበርካታ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን በስፍራው የተቀመጠው ታሪክ ያስረዳል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በገዳሙ ውስጥ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ከአንድ ዕለት የተፈለፈለ ዋሻ ቤተክርስትያን፣ ከ15 በላይ የውኃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን፣ የወለቃ ድልድይን በመሥራታቸው የህንጻ ባለሙያ ሊቅ እንደነበሩ በታሪካቸው ላይ ተፅፎ ይገኛል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በደራሲነት ከፃፏቸው 40 በላይ መጻሕፍት መካከል “መጽሐፈ ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት፣ ሆህተ-ብርሃን፣ ጸሎተ ፈትቶ ዘቅዳሴ ቁርባን” ይገኙበታል፡፡

በገዳሙ በዚህ ወቅት ‹‹የውኃ ማቆር ቴክኖሎጅ›› ተብሎ አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለው በጋስጫ ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ላይ የዋለ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ለገዳሙ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡

በዚህ ቦታ የቅርስ ቁጥጥርና መዝገባ ለማድረግ በመንግሥት በኩል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ጥቅምት 3/2012 ዓ.ም የዚህ ስፍራ ቅርሶች ያሉበትን ደረጃ ለማሳወቅ የክትትልና ምዝገባ ሥራ እንደሚጀመር የከላላ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ መስፍን ዋሲሁን አስታውቀዋል፡፡

በመንገድ መሠረተ ልማት በኩል ከከላላ – ቆርኪ – አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ድረስ አንደኛ ደረጃ ገጠር መንገድ ያለው ነው፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ክብረ በዓላትን ጠብቀው ጥቅምትና ጥር ወር ላይ የሚገኙ ጎብኚዎች በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ፍሰት ደካማ እንደሆነ ባለሙያው ነግረውናል፡፡ ወረዳው በሚገኙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች እና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የማስተዋወቅ ሥራ ቢሰራም የዞኑም ሆነ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ተቋማት የሚጠበቅባቸውን እየሠሩ አይደሉም፡፡ በቅርስነትም አልመዘገበም የሚሉት ባለሙያው የማስተዋወቅ ሥራ በተለይ ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ አይደለም፤ የወረዳው በጀት መጠነ ሰፊ ማስታወቂያ ለመሥራት አያስችልም፡፡

እንደ ጣና ሐይቅ፣ ላልይበላና ሌሎች ቅርሶች በመርሀ ግብራቸው ሲያስተዋውቁ ‹‹ይህም ብዙ ዘመን ያስቆጠረ ጥንታዊ ቅርስ በመሆኑ እንዲያስተዋውቁ ጥረት ተደርጓል ግን አልተሳካም›› ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ቅርስ ምዝገባ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ደመቀ ማስተዋወቅ ማለት ያለንን ሀብት መሸጥ ነው፡፡ ከዚህ ተግባር በፊት ግን የውጭ ጎብኚ ስቦ ገቢ ለመሰብሰብ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት መሟላት አለበት፤ ይህ ቱሪዝሙ የሚፈልገው ነገር ነው፡፡ ባለሙያው እንደተናሩት እንደ መብራት፣ ውኃ፣ ኔትወርክና ሌሎችንም መሠረተ ልማቶች ለማሟላት ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በዕቅድ በመግባቢያ ሰነድ በታገዘ መልኩ በቅንጅት መሠራት ይኖርበታል፡፡

‹‹ ይህንንም በዕቅድ አፈፃፀምና ትውውቅ ዝግጅት ላይ ሳይቀር ለክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አሳውቀናል›› ያሉት አቶ ብርሃኑ ደመቀ በገዳሙ አቅራቢያ የውጭ ጎብኚዎችን ሊያረኩ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሌሉ አስረድተዋል፡፡ ባለሀብቶችም ገብተው እንዲያለሙ የማድረግ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት፡፡

በገዳሙ ቤተ መዘክር ለመገንባት መነሻ የሚሆን 170 ሺህ ብር ተለቅቆ እንደነበርና ገንዘቡ ሌላ ግዥ ተፈፅሞበት ባክኖ እንደቀረም አስታውሰዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleአሜሪካ በአፍጋኒስታን በፈጸመችው ጥቃት 30 አርሶ አደሮችን መግደሏን አመነች፡፡
Next articleትዊተር በስድስት ሀገራት ከ10 ሺህ በላይ አድራሻዎችን መዝጋቱን ገለጸ፡፡