
ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት እየተገነባ የሚገኝ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተር ሀይሉ አብርሃም ባለፉት 11 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ነግረውናል፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት ከተሰበሰበው በቀዳሚነት እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡ እስከዚህ ወቅት የተሰበሰበው ደግሞ 15 ቢሊዮን 597 ሚሊዮን ብር መድረሱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በነበረው ተሳትፎ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ እንደማያውቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ በዲፕሎማሲ ድርድሩ ላይ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የሕዝብ ቁጭት መፍጠሩ፣ ውኃ ሙሌቱን ተከትሎ በሕዝቡ ላይ መተማመን መፈጠሩ፣ መንግሥት በግድቡ ላይ የሚያደረገውን የድርድር ሂደት እና ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው ለሕዝብ ማድረሱ ለድጋፉ ማደግ በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡
በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ ተሳትፎም ከፍተኛ እንደነበር አቶ ሀይሉ ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 95 ሚሊዮን የሚኾነው ከውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተሰበሰበ መኾኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከዚህ በፊት ከዲያስፖራው ከተሰበሰበው ገንዘብ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ተብሏል፡፡
አቶ ሀይሉ እንዳሉት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተደረገው ድጋፍ የዕድሜ እና ኑሮ ልዩነት ያልታየበት፣ ከልጅ እስከ አዋቂ የተሳተፉበት ነበር፡፡
የምሁራን ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት እንደነበርም አቶ ሀይሉ ነግረውናል፡፡ በተፋሰስ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለመሥራት እንቅስቃሴ የተጀመረበት ጊዜ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በጨለማ የሚኖረውን የኀብረተስበ ክፍል ከችግር ለማውጣት እና በጭስ ጉዳት የሚደርስባቸው እናቶችን ለመታደግ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ግብርናን ለማዘመን እና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ በመኾኑም ኢትዮጵያውያን ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሀገሪቱ በቀጣይ የምታከናውናቸው የልማት ሥራዎችን ለማሳካት ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ