
የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን መሰረት አድርጎ አንድ ቢሊየን ችግኝ በጎረቤት ሀገራት ለመትከል መታቀዱን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ10 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በተለይም በመጀመሪያው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር ብቻ 353 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ችግኝ በመትከል በዓለም ክብረ ወሰንነት መመዝገቡ ይታዎሳል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ ተጀምሯል፡፡ በ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሀገር ውስጥ 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሀገር ውስጥ ከሚካሄደው የችግኝ ተከላ በተጨማሪ ቀጣናዊ ሽግግርም እንዲኖረው ታቅዷል ነው የተባለው፡፡ የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን መሰረት አድርጎ አንድ ቢሊየን ችግኝ በጎረቤት ሀገራት ለመትከል መታቀዱም ተጠቁሟል፡፡
ቀጣናዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለሀገራቱ የጋራ ትብብር እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ሚናው የጎላ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለይም ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ ቀጣናዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአባይ ተፋሰስን ማዕከል ያደረገ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና መርሐ ግብሩ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ቀጣናዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ የተከተለ መኾኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ “ቀጣናዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሽሚያ ሳይኾን አብሮ የማደግ መርኾ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ጀምሮ በአፍሪካ ሀገራት ሕብረት ላይ የማይናወጥ አቋም እንዳላት ጠቁመዋል፡፡ ቀጣናዊው ትብብር እና አብሮ የመልማት ጥረቱ ወደ አህጉራዊ ደረጃ ለማሸጋገር ይሠራልም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ