
“የፌዴራል መንግሥት የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይዟል” የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከመተከል ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ከሰሞኑ መግለጹን አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ዜጎች በመፈናቀላቸው በሰባዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ችግር አስከትሎ አልፏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዞኑ ኮማንድ ፖስት፣የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከተፈናቃዮች ጋር በአደረጉት ተደጋጋሚ ውይይት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ሕይወት እንዲመሩ እየተደረገ ነው፡፡
የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ በትግሉ ተስፋሁን ለአሚኮ እንደተናገሩት በቻግኒ ራንች ጊዚያዊ መጠለያ የነበሩ ተፈናቃዮች ሙሉ ሙሉ ተመልሰዋል፡፡ ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ዜጎችም እስከ አሁን ድርስ የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብና ሌሎች ቁሶችን በማቅረብ ቀና ትብብር እንዳደረጉላቸው ጠቁመዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ረጂ ድርጅቶችና መንግሥት ለተፈናቃዮች ዕለታዊ ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ ለተፈናቃዮች የዕለት ምግቦችን ከማድርስ ጎን ለጎን የአካባቢው ባሕልና ሥርዓት በሚፈቅደው አካሄድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የሀገር ሽማሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የእርቅ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ እንደኾነም አቶ በትግሉ ተናግረዋል፡፡ የእርቅ ሥነ ሥርዓት መደረጉ ከዚህ በፊት ከነበረው ቂም በመውጣት ነዋሪዎች ወደ ልማት ሥራ እንዲገቡ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮች በአካባቢያቸው ተረጋግተው እንዲኖሩ 24 ሰዓት በመከላከያ ሰራዊት ጥበቃ እየተደረገላቸው መኾኑን የነገሩን አቶ በትግሉ በሚኖሩበት አካባቢ የጸጥታ ስጋት እንደሌለባቸው አስረድተዋል፡፡
ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች መሠረታዊ የመጠለያ፣የመጸዳጃ፣የውሃ እና የሕክምና አገልግሎት እንደተሟላላቸውም ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮች አሁን ላይ በአራት ማእከላት ማለትም ዳንጉር፣ብሎን ፣ድባጤ እና ማንዱራ መኖር ጀምረዋል::
ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎች በማእከላት ኾነው የእርሻ ሥራ መጀመራቸውን አቶ ብትግሉ ነግረውናል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትራክተሮችን በማቅረብ እያገዙ እንደኾነም ተገልጿል፡፡
በቀጣይ ዜጎች በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ ድርስ የሁለቱ ክልል መንግሥታት የጋራ ግብረኀይል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም በመተከል ዞን የጋራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ይቋቋማል ብለዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱም ተፈናቃዮች ወደ መደበኛ ሥራ እስከሚገቡ ድርስ እየተከታተለ ችግሮችን ይፈታል፣የማስተካከያ እርምጃም ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
የፌዴራል መንግሥትም ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ለመደገፍ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ መበጀቱም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ