ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን የሚያስተሳስረው የ ‘ላፕሴት’ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን በጋራ መሥራት ይገባል” አፍሪካ ኅብረት

208

“ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን የሚያስተሳስረው የ ‘ላፕሴት’ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን በጋራ መሥራት ይገባል” አፍሪካ ኅብረት

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት ለማስተሳሰር ያለመው የላፕሴት ፕሮጀክት አህጉራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ለፕሮጀክቱ ስኬት ሁሉም እንዲረባረብ አፍሪካ ኅብረት ጥሪ አቀረበ።

የላፕሴት ፕሮጀክት በፍጥነት መንገድ፣ ባቡርና ሌሎች ግዙፍ መሰረተ ልማቶች አማካኝነት ሶስቱን ሀገሮች የማስተሳሰር ውጥን የያዘ ነው።

ፕሮጀክቱን በሚመለከት የሀጋራቱ የዘርፉ ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል።

የቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማት ልዩ ልዑክ ራይላ ኦዲንጋ በዚሁ ጊዜ ፕሮጀክቱ ቀጠናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የተለያዩ የእድገት ምዕራፎች እንዳሉት ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላለው ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚያዊ ውህደት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እንደ ‘ላፕሴት’ ያሉ የትስስር መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ያስፈልጉታል ብለዋል።

ይህም አህጉሪቱ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሰዎች ነጻ ዝውውር እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ነው የአፍሪካ ኅብረት ልዑኩ ራይላ ኦዲንጋ የገለጹት።

የላፕሴት ፕሮጀክት ሦስቱን ሀገራት በትራንስፖርት በማስተሳሰር ረገድ የያዘውን ውጥን እውን እንዲሆን ሁሉም የዘርፉ ተዋንያኖች በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኬንያ ቀጣናዊ የልማት ትስስር ሚኒስትር አዳን ሞሃመድ በበኩላችው “ፕሮጀክቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ ቀጠናዊ ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል” ብለዋል።

ይህን በማድረግም ፕሮጀክቱ የዘረዘራቸውን አካባቢያዊ የኢኮኖሚ እቅዶች ማሳካት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ የቀጣናው ሀገራት ያላቸውን የኢኮኖሚ ትስስር በማጠናከር እድገታቸውን ያፋጥንላቸዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።

የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውና በቅርቡ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ የተከፈተው የላሙ ወደብ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ በማስፋት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

የላፕሴት ፕሮጀክት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ነበር በሦስቱ ሀገራት መሪዎች የጋራ ሥምምነት ወደ ሥራ እንዲገባ ውሳኔ የተላለፈው። ኢዜአ እንደዘገበው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleኢትዮጵያ እና ጆርዳን ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
Next articleየትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቀረበ።