
ኢትዮጵያ እና ጆርዳን ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያፈልግ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የጆርዳን አምባሳደር ዋፊ አያድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አቶ ደመቀ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያፈልግ አንስተዋል። ተሰናባቹ አምባሳደር ግንኙነቱን ለማጠናከር ላበረከቱት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተም በተለይም በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንዲሁም የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ አቶ ደመቀ ለአምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህደሴ ግድብን በተመለከተ በአረብ ሊግ በኩል የተያዘውን ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም በተለመከተ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። ዓባይ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያም የዓለም አቀፍ ሕግን መሰረት በማድረግ ግድቡን የምትገነባ መሆኑን አስረድተዋል። ጆርዳን እንደ ወዳጅ ሀገር አዎንታዊ ሚና መጫወት የሚጠበቅባት እንደነበርም አንስተዋል።
አምባሳደር ዋፊ አያድ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጆርዳን የቀጥታ በረራ ቢጀመር አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆን አንስተዋል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ቆይታ በመንግስት በኩል ለተደረገላቸው ድጋፍ እና ትብብር ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ትስስር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m