ፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ-ምርጫ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆን ተጠየቀ፡፡

85
ፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ-ምርጫ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆን ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ-ምርጫ ወቅት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆን ተጠየቀ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ የቅድመ-ምርጫና የምርጫ ወቅት ሰላማዊ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል።
ፓርቲዎች ሀገር ከፖለቲካ በላይ በመሆኗ ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም የሕዝብን ድምጽ አክብረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው መክረዋል።
እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ገለጻ፤ ፖለቲካን የሰውን ህይወት ለመቀየር በመጠቀም በሰለጠነ መንገድ የሕዝብን ድምጽ አክብሮ መንቀሳቀስ ይገባል። ቀደም ሲል ከነበሩ የድህረ-ምርጫ ኹነቶች በመማር ሀገርና ሕዝብን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በቅድመ-ምርጫና በምርጫ ወቅት የተስተዋለውን ሰላም ለማስቀጠል ፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ በሚሆንበት ወቅትም ደጋፊዎቻቸውና አባሎቻቸውን ኃላፊነት በተሞላ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከሚናገሩት ቃላት ጀምሮ የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩና የሀገርን ሰላም የሚያስቀጥሉ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።
May be an image of 1 person, sitting and suitየምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በበኩላቸው በምርጫው የተወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ያሳዩት ሥነምግባር ከሞላ ጎደል የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት ሦስት ዓመታት መሻሻል ማሳየቱን የሚያመላክት መሆኑን ነው የገለጹት።
“በምርጫው ዕለት ሕዝብ ድምጽ ለመስጠት ላሳየው ትዕግስት ክብር በመስጠት በድህረ- ምርጫ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ መሆን ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ አክለዋል።
የዴሞክራሲን መንገድ ለማስቀጠል የሕዝብ ውሳኔ ማክበር የመጀመሪያው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ውጤቱ ይፋ ሲሆን የሕዝብን ድምጽ ማክበር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሕዝብ ምርጫ ቢያደርግም ድምጹን በትክክል ማግኘት አለመቻሉን አውስተው፤ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየውን አዲስ ታሪክ ለማስቀጠል በኃላፊነት መሥራት እንደሚጠይቅ ነው ያብራሩት። ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleእስካሁን 378 ምርጫ ክልሎች ውጤታቸውን ቦርዱ ላቋቋመው የውጤት አጣሪ ቡድን ማስረከባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
Next articleኢትዮጵያ እና ጆርዳን ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡