
ባህላዊ ህክምና በጤና ዘርፉ ውስጥ ሕጋዊ ሥርዓት ይዞ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 60 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የባህላዊ ህክምናን እንደሚጠቀም መረጃዎች
ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 90 በመቶ የሚጠጋ ሕዝብ ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ ባህላዊ ህክምናን እንደሚጠቀም
ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል። በሚኒስቴሩ የባህላዊ ህክምና ቡድን አስተባባሪ ወይዘሪት እህተማሪያም ሻምበል
በኢትዮጵያ የባህላዊ ህክምና የቆየ ታሪክ ቢኖረውም በጤና ሥርዓቱ ውስጥ ወጥ አሠራር ሳይዘረጋለት መቆየቱን ተናግረዋል።
ጤና ሚኒስቴር ዘርፉ ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ በሕግና ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ ቡድን አቋቁሞ
እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ ዘርፉን የሚመለከት የአስር ዓመት እቅድ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ በእቅዱ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ቅድሚያ
በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በግንዛቤ ማስፋት፣ የባህላዊ ህክምና አዋቂዎችን አቅም ማጎልበት፣ ተመራማሪዎችና የባህላዊ ህክምና አዋቂዎች አብረው
መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ጥናትና ምርምር ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ተጠቃሾ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች የምርምር ማእከላት በዘርፉ የሚያደርጉትን ምርምር መደገፍ ሌላኛው የትኩረት
አቅጣጫ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡በተጨማሪም ባህላዊ መድኃኒቶችን ከመጠቀም በፊት መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች
ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
ባህላዊ ህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ ሕጋዊ ሆኖ ምዝገባ የተጀመረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከዚያ
በኋላ ባሉ ጊዜያት ዘርፉን ወጥ በሆነ ሥርዓት ከመምራት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት
የባህላዊ ህክምና የሚሰጡ አዋቂዎች ብዛት ምን ያህል እንደሆኑ በትክክል አይታወቁም ብለዋል።
መረጃ ማደራጀትና በዘርፉ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን መለየት በእቅዱ የአምስት ዓመት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ
እንደተካተተ አንስተዋል። የእቅዱ ተግባራዊነትም ባህላዊ ህክምና በጤና ዘርፉ ውስጥ ሕጋዊ ሥርዓት ይዞ ቀጣይነት ባለው
መልኩ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m