
ሠራዊቱን መከታ በማድረግ ፍላጎታቸውን ማስፈፀም ለሚፈልጉ የፖለቲካ ሕልመኞች ሠራዊቱ መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስቡ።
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌድሪ ምዕራብ ምድብ አየር ኃይል የተሟላ የመሥሪያ ሕንጻውን ዛሬ አስመርቋል።
የኢፌድሪ አየር ኃይል ምዕራብ አየር ምድብ ኃላፊ ኮሎኔል ቸርነት መንገሻ “24 ሰዓት የአየር ክልሉንና ሕዋውን ጥበቃ ለማድረግ በቴክኖሎጂና በዕውቀት እየተሻሻለ ነው” ብለዋል።
ኮሎኔል ቸርነት የምድቡ ማስፋፊያ ግንባታ ስር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ላይ ላለው መከላከያ ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በሚግ 23 ቅርፅ የተሠራው አዲሱ የማስፋፍያ ሕንጻ በርካታ ወታደራዊ አገልግሎቶችን ያቀፈ እንደሆነም ተነግሯል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በክልሉ አንፃራዊ ሠላም እንዲሰፍን መከላከያ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን አንስተው አመሥግነዋል።
አቶ ተመስገን መከላከያው በፖለቲካ ልምሻ ምክንያት ከተፈጠረው የመንደር ስምሪት ወጥቶ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ሠራዊቱን መከታ በማድረግ ፍላጎታቸውን ማስፈፀም ለሚፈልጉ ሕልመኞች ሠራዊቱ መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበትም ነው ያሳሰቡት።
“የፖለቲከኞች በሐሳብ በተለያዩ ቁጥር መሳሪያ አስነግቶ በሕዝብ ላይ ጥይት ማስተኮስ ነውረኛ ተግባር በመሆኑ ሠራዊቱ የሌላ ፖለቲካ ተሸካሚ ከመሆን ራሱን ሊጠብቅ ይገባል” ብለዋል።
የኢፌድሪ አየር ኃይል ምዕራብ አየር ምድብ
የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ሆኖ የሀገሪቷን ሕዋና የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት በአስተማማኝነት መጠበቅ ራዕይ ያደረገ ነው።
ማዕከሉ ከአየር ክልልና ሕዋ ጥበቃ በተጨማሪ የኤሌክትሮኒክስ ደኅንነትን እና የሳይበር ተጋላጭነትን ለመከላከልና ለመመከት የሚሠራ ነው።
የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ይልማ መርጋሳ እና የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዥር ሹም አደም መሀመድ በምረቃው ተገኝተዋል።
ዘጋቢ ፦ ግርማ ተጫነ