
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማሻሻያዋ እያደረገች ያለችዉ አንዱ ለዉጥ የሀገር በቀል ምርቶችን በግብዓትነት መጠቀም እንደኾነ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከምግብ ዘይት አምራቾች ጋር ምክክር እያካሄደ ነዉ። የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከፌዴራል፣ከክልል የሥራ ኀላፊወች፣ከባለድርሻ አካላት፣ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ተወካዮች ጋር ነው ምክክር እየተደረገ የሚገኘው፡፡
ምክክሩ “የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ፍላጎት በሀገር ዉስጥ ለመተካት እንሠራለን” በሚል መሪ ሀሳብ ነዉ እየተካሄደ ያለዉ፡፡
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንዳሉት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማሻሻያዋ እያደረገች ያለችዉ አንዱ ለዉጥ የሀገር በቀል ምርቶችን በግብዓትነት መጠቀም ነዉ፡፡ በዚህም ስንዴ እና ዘይትን በሀገር በቀል ግብዓት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታዉን ለመሸፈን እየተሠራ ነዉ ብለዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸዉ ወደ ሥራ ቢገቡ የኑሮ ዉድነቱን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጅ በኢንዱስትሪዎቹ ላይ የግብዓት አቅርቦት ችግር ማነቆ ኾኗል ያሉት አቶ መላኩ በተለይ የቅባት እህሎች ምርት ዝቅተኛ መኾንን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ እንደተገለጸው በምግብ ዘይት ላይ የተሰማሩ 232 የሚደርሱ ኢንዱስትሪወች አሉ፡፡ ከእነዚህ ዉስጥ 26 መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ሲኾኑ 206 ደግሞ በአነስተኛ ደረጃ ያሉ ናቸዉ፡፡
የዛሬዉ ምክክር የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የሚያግዝ ሀሳብ ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የምክክሩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጺዮን አበበ-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ