
ባለፉት ወራት ከሰምንት ሀገራት 25 ሺህ 472 ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ተመላሽ የሆኑ ዜጎችን ጉዳይ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በዋናነት ደግሞ ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር፣ ለሰላም ሚኒሰቴር ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት (አደጋ ሰጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የኢሚግሬሽንና ወሳኝ ኹነቶች ኤጀንሲ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ)፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት እስከ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም ድረስ ከስምንት ሀገራት 25 ሺህ 472 ዜጎች ተመልሰዋል፡፡ የተመለሱ ኢትዮጵያውያንን ተቀብሎ በማስተናገድ፣ በቆይታ ወቅትና ወደ መኖሪያ ስፍራዎች ሲጓጓዙ አስፈላጊውን ወጪ በመሸፈን ከቤተሰብ ጋር ማቀላቀል መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የመልሶ ማቋቋም ተግባራት በየደረጃው በሚገኙ አሰተዳደር አካላት አማካይነት በመከናወን ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በቅርቡም በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎችንን ሁኔታ ላይ ምላሽ ለመስጠት ወደ ሳዑድ አረቢያ የተጓዘው የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በጋራ በተሠራው ሥራ ዜጎችን በየዕለቱ የማጓጓዝ፣ በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ማሳረፍ፣ የምግብና አልባሳት አቅርቦት፣ ሂደቱን ያጠናቀቁትን የትራንስፖርት ወጭያቸውን ሸፍኖ ወደ ቤተሰብ የመሸኘት ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት። ከትናንት ምሽት ጀምሮ ከሳዑዲ አረቢያ 3 ሽህ 691 ዜጎች መመለሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ ቀናትም ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ