ከአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

749

ከአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 20/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞ ደብረብርሃን ተማሪዎች በጎ አድራጎት ኅብረት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርሲቲ ለተመደቡ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

የህብረቱ ሰብሳቢ ዶክተር እሸቱ በቀለ እንደገለፁት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር በጉዳት ውስጥ ሆነው በሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ህብረቱ ድጋፍ አድርጓል።

የተማሪዎቹ ቤተሰቦች በጸጥታ ችግር ምክንያት ንብረት የወደመባቸው በመሆኑ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመላክ የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ለማቃለል ድጋፉ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ በችግር ወቅት የመደጋገፍና የመተጋገዝ ባህልን ለወጣቶች ለማስተማር ጭምር የተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 12 ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለአንድ ዓመት የሚሆናቸው ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ለሌሎች 170 ተማሪዎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 1 ሺህ 250 ብር የትራንስፖርትና ለሌሎች ወጭዎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከአጣዬ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰላም የምሩ ድጋፉ ወቅታዊ ችግሯን እንደሚያቃልልላትና በትምህርቷ ለውጤት እንድትበቃ አቅም እንደሚፈጥርላት ተናግራለች።

ተማሪ አዲሱ አብተው በበኩሉ በወቅታዊ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን ሁኔታ በመገንዘብ በጎ ፈቀደኞች የትምህርት ወጪያቸውን መሸፈናቸው እንዳስደሰተው ገልጿል።

ከተደረገው ድጋፍ በላይ በችግር ወቅት ፈጥኖ የሚደርስና ችግሩን የሚጋራ ወገን እንዳለ ማረጋገጡ በትምህርቱ እንዲበረታ መነሳሳት የፈጠረለት መሆኑንም ተናግሯል።

ተማሪዎቹ አእምሯቸውን አረጋግተው ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉና ከሌሎች አቻ ተማሪዎች ጋር በአንድነትና በፍቅር ተስማምተው እንዲማሩ ለማስቻል በማህበሩ አባላት የግማሽ ቀን የስነ ልቦና ትምህርትም ተሰጥቷል። ኢዜአ እንደዘገበው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበመዲናዋ የሚገነበው የአማራ ባህል ማዕከል አልማ ለሚያከናውነው የልማት ስራ አጋዥ እንደሚሆን ተገለጸ።
Next articleባለፉት ወራት ከሰምንት ሀገራት 25 ሺህ 472 ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡