
የእምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ ከዘመቻ ሥራዎች የተሻገረ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 20/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በ3 ሺህ 672 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ ተንጣሎ የተዘረጋው ጣና በኢትዮጵያ በስፋቱ ቀዳሚው ሐይቅ ነው፡፡ ጣና ከሰሜን ወደ ደቡብ 84 ኪሎ ሜትር እና ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ደግሞ 66 ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተደጋጋሚ የጥናት ውጤቶች የሐይቁ አማካይ ጥልቀት 9 ሜትር ሲኾን ከፍተኛው ደግሞ እስከ 14 ሜትር እንደሚደርስ ይታመናል።
የጣና ሐይቅ ተፈጥሯዊ ውበት እና ብዝኃ ሕይዎት ብቻውን ጎብኝዎችን የማማለል ድንቅ አቅም ቢኖረውም በውስጡ ያቀፋቸው ጥንታዊ አድባራት፣ ገዳማት እና ደሴቶች ደግሞ ተጨማሪ ግርማን አላብሰውታል፡፡ ከዓመታት በፊትም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንቃድንቅ መዝገብ ውስጥ ተካቷል፡፡
የጣና ሐይቅ 30 ለሚጠጉ አስደናቂ ገዳማት እና ደሴቶች መሰረት ነው። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ወይም የፍሬምናጦስ መቃብርን ጨምሮ የአፄ ዳዊት፣ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የአፄ ሱስንዮስ፣ የአፄ ፋሲል እና ሌሎች ነገስታት አጽም በክብር ያረፈው በሐይቁ ውስጥ በሚገኙ ገዳማት እንደኾነ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ያክል በጣና ሐይቅ ገዳማት ውስጥ በመቀመጥ የጻፈው ምልክት አልባ የድጓ መጽሐፉን ጨምሮ የእጅ መስቀሉ እና ከሐር የተሠራ ካባው የሚገኙትም በዚሁ በጣና ሐይቅ ላይ በሚገኙት ገዳማት ውስጥ ነው።
ጣና ውሃ ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳንም ጭምር ነው ፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሐይቁ ላይ የተከሰተው መጤ የእምቦጭ አረም ለሐይቁ የህልውና አደጋ መኾኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት መንግሥት፣ ማኅበራት፣ ግለሰቦች እና የበጎ አድራጎት ተቋማት የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ርብርብ ቢያደርጉም መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣት የሐይቁን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
ከጥቅምት 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ እምቦጭን በሁለት የተቀናጀ መንገድ ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ያሉን የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ የመጤ እና ተስፋፊ አረሞች መከላከል ተወካይ ዳይሬክተር መዝገቡ ዳኛው ናቸው፡፡ በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች እና 30 ቀበሌዎች የእምቦጭ አረም መከላከል ሥራ ተሰርቷል ያሉት አቶ መዝገቡ ከእነዚህ ውስጥ ለማሽን እንቅስቃሴ የሚመቹት አምስት ቀበሌዎች ብቻ ነበሩ ብለዋል፡፡ በቀሪዎቹ ቀበሌዎች አረሙን በሕዝብ ጉልበት ለማስወገድ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
አረሙ 90 በመቶ ከሐይቁ ላይ መነሳቱን የገለጹት ተወካይ ዳይሬክተሩ አበባ እና ፍሬ ሳያፈራ በመታረሙ በሚቀጥለው ዓመት የሚኖረው ስርጭት በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ አረሙን ለማስወገድ ከአንድ ሰሞን የዘመቻ ሥራ በመውጣት በየጊዜው ክትትል ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በያዝነው ዓመት የፌዴራል መንግሥት ተቋማት እና በገንዘብ፣ኢኮኖሚና ትብብር ሚኒስቴር እስከ 70 ሚሊየን ብር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የገለጹት አቶ መዝገቡ በቀጣይ የተቀናጀ የቴክኒክ እና ሙያ ድጋፍም ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት በትብብር አረሙን ከሐይቁ ላይ ለማስወገድ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
በምርጫ ሥራዎች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረውን አረም የማጽዳት ሥራ በቀጣይ ሳምንት ይጀመራል ብለዋል አቶ መዝገቡ፡፡ የእምቦጭ አረምን ከሐይቁ ላይ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከዘመቻ ሥራ የተሻገረ ርብርብ ያስፈልጋል ያሉት አቶ መዝገቡ የክልሉ መንግሥት የተሠሩ ሥራዎችን በመከታተል እና አቅጣጫ በመስጠት እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m