
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ባሕር ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፤ ነገር ግን ለሜቴክ በዱቤ የሰጠው የ2 ቢሊዮን ብር ዱቤ አገልግሎት እንዳልተከፈለው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለፈው የበጀት ዓመት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ፡፡ የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንዳስታወቁት ባለፈው ዓመት አማካይ የኮንቲነር የወደብ ቆይታ 6 ቀን ከ6 ሰዓት ነበር፡፡
የአገሪቱን ወጭና ገቢ ንግድ ከማሳለጥ አኳያ ስለተጨማሪ ወደቦች ወደ ሥራ መግባት ሲናገሩም ‹‹የአሰብ ወደብን በሚመለከት የኢትዮጵያ ባሕር ሎጂስቲክስ አገልግሎት መረጃ የለውም›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለፈው ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ዕቃ ያጓጓዘ ሲሆን በ2012 የበጀት ዓመት ደግሞ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ዕቃ ለማጓጓዝ ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
የዱቤ አገልግሎት የሚሰጠው ባሕር ትራንስፖርት ገልግሎት ድርጅት ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሰጠው የ2 ቢሊዮን ብር ዱቤ አገልግሎት እንዳልተከፈለውም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ከትራንስፖር ሚኒስቴር ወጥቶ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ስር የሚገኝ ሲሆን ወደግል የማዞር ሥራው ደት ላይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅት 9 ሁለገብ እና 2 ነዳጅ ጫኝ በድምሩ 11 ንብረትነታቸው የድርጅቱ የሆኑ መርከቦች ያሉት የኢትዮጵያ ባሕር ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከ50 በላይ ደግሞ በኪራይ የሚሠራባቸው መርከቦች አሉት፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በማያውቀው ሁኔታ የነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ ለኢትዮጵያ ነዳጅ እያመላለሱ አይደሉም፡፡
ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን -ከአዲስ አበባ