የሕዝብን ድምጽ አክብሮ በመቀበል ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር እንደሚገባ የአማራ ሴቶች ማኅበር ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

148
የሕዝብን ድምጽ አክብሮ በመቀበል ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር እንደሚገባ የአማራ ሴቶች ማኅበር ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝቡም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጠቃለለ ውጤት እስኪገለጽ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ እንደሚገባ ፌዴሬሽኑ ዛሬ በሰጠው በግለጫ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ሴቶች ማኅበር፣ የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን እና የአማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የአማራ ሴቶች ማኅበር ጸሐፊ ወይዘሮ ትጥቅነሽ ዓለሙ ማኅበሩ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የጎላ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ በምርጫ ቦርድ የተሠጠውን የማስተማር እና የመታዘብ ኀላፊነት በአግባቡ ተወጥቷል ብለዋል፡፡ የአማራ ሴቶች ማኅበር በክልሉ ካሉ ሁሉም ዞኖች 1 ሺህ 855 አባላትን በመመልመል ለምርጫ ታዛቢነት አሠማርቶ እንደነበር ወይዘሮ ትጥቅነሽ አንስተዋል፡፡
ወይዘሮ ትጥቅነሽ እንዳሉት የተመለመሉ አባላት ከምዕራብ ጎንደር፣ ከማዕከላዊ ጎንደር እና ከደቡብ ወሎ በስተቀር በሁሉም ዞኖች የመታዘብ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ታዛቢዎቹ በተመደቡባቸው ጣቢያዎች ቀድመው በመገኘት ማኅበረሰቡ ሳይጉላላ ድምጽ የሰጠበትን ሁኔታ ታዝበዋል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ጥቃቅን ችግሮች ሲያጋጥሙ ከሌሎች ታዛቢዎችና ከምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በመወያየት ችግሩ የሚፈታበትን ሁኔታ በማመቻቸት ኀላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብለዋል በመግለጫው፡፡
ጸሐፊዋ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም ታዛቢዎቹ ችግሩን ተቋቁመው ቆጠራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በቦታው በመገኘት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ገልጸዋል፤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ያሳተፈ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ወይዘሮ ትጥቅነሽ ሕዝቡ ድምጹን ለመረጠው ፓርቲ ሳይሸማቀቅ የሠጠበት ምርጫ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ድምጽ ማክበርና ለሀገራዊ አንድነት በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ እመቤት ምትኩ ፌዴሬሽኑ በስሩ የሚገኙ የአባል ማኅበራትን አባላት በመመልመል 1 ሺህ 745 አባላትን በታዛቢነት ማሳተፉን ተናረዋል፡፡ የአማራ ሴቶች ማኅበር፣ የአማራ ሴት ደራሲያን ማኅበር፣ የአማራ ሴት ነጋዴዎች ማኅበር አባላት እና የአማራ ሴት አካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የጽሕፈት ቤት ኀላፊዋ ገለልተኛ ታዛቢዎችን ለመመልመል የወጣው መስፈርት ከባድ በመሆኑ ሠፊ ጊዜ መውሰዱን ጠቁመዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና ድኅረ ምርጫ ምን መሥራት እንዳለበት አቅዶ በመንቀሳቀሱ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል ነው ያሉት፡፡ ፌዴሬሽኑ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ከምርጫ ቦርድ የተሰጠውን የመታዘብ ኀላፊነት በብቃት ለመወጣት ጥረት አድርጓል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ እመቤት ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ የሄደበት ርቀት የሚመሰገን ቢሆንም የባጅ መዘግየት የሥም እና የፎቶ ግራፍ መለያየት በቀጣይ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ እመቤት ሕዝቡም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጠቃለለ ውጤት እስኪገለጽ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም “እኔ የተወዳደርሁበት ወይም እኔ የመረጥሁት የፖለቲካ ፓርቲ ለምን አላሸነፈም” ከሚል የተሳሳተ እሳቤ መውጣት ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን ማኅበር 489 አባላትን በምርጫ ታዛቢነት ማሳተፉንም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የጋራ ማንነት ላይ መሥራት እንደሚገባው ተጠቆመ
Next articleምርጫ ከተካሄደባቸው 440 የምርጫ ክልሎች መካከል 221 የምርጫ ክልሎች ውጤት መለጠፋቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡