አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የጋራ ማንነት ላይ መሥራት እንደሚገባው ተጠቆመ

128
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የጋራ ማንነት ላይ መሥራት እንደሚገባው ተጠቆመ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫው አሸንፎ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የጋራ ማንነትን ለማምጣት መሥራት እንደሚጠበቅበት የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ገለጹ።
የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በምርጫ በሕዝብ ድምጽ አሸንፎ መንግሥት የሚመሰርተው ፓርቲ የኢትዮጵያን ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች በትክክል መረዳት የመጀመሪያ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ መክረዋል። ቀደም ሲል አንድነትን የሚያናጥቡና ልዩነትን የሚያሰፉ ጉዳዮች ላይ ሲሠራ መቆየቱን አንስተው ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶች ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሀገራዊ ምርጫና አዲስ ከሚመሰረተው መንግሥት የሚጠበቁ ሥራዎችን አስመልክቶ ኢዜአ ከምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ እና ከሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ጋር ባደረገው ቆይታ ነው ምክትል ዳይሬክተሩ የገለጹት።
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት በሀገር ውስጥ የሚስተዋሉ ግጭቶችን፣ ከልማት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ የብሔርና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ መግባባት ላይ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሕዳሴ ግድብን አይነት አንድ የሚያደርጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመቅረጽ በምርጫ የተጀመረውን አንድ እርምጃ በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ማበልጸግ መሄድ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊነት እንደ ጋራ ማንነት የራሱ ምሰሶ ኖሮት እንዲገነባ በትምህርትሥርዓቱና በሌላም መንገድ ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚደርስበትን አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ዶክተር ብርሃኑ ገልጸዋል። ዜጎችም በድምጻቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ፓርቲዎች የሚጠብቋቸው የተለያዩ ፍላጎቶች ስለሚኖሯቸው በዚያው ልክ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ውስጣዊ ችግሮችን በዚህና በሌሎች ፖሊሲና አሠራሮች በመፍታት ውጫዊ ተጽዕኖን ለመቋቋም በተሻለ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር መመከት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በተግባር ለውጥ እንዲያመጡ “ጥሩ መንግሥት” ያስፈልጋል በማለት ጥሩ መንግሥት የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ የሚችል መሆኑንም አመልክተዋል።
የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶም የሚመሰረተው መንግሥት ሕዝብ የሰጠውን ድምጽ አክብሮ እንዲሠራ ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል ብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ሕገ-መንግሥት ማሻሻልን ጨምሮ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የጋራ ማንነት ላይ መሠረት በማድረግ መሥራት ይጠቅበታል።
በምርጫ የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫና በምርጫ እንዲሁም ከምርጫ በኋላ ያሳዩትን የዴሞክራሲ መሻሻል ባሕል አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ ሲደረግም ሀገርን በማስቀደም ሕዝብ የሰጣቸውን ውጤት በፀጋ መቀበል እንደሚገባቸው መክረዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የወተት ምርትን 50 በመቶ የሚቀንሰውን ጉርብርብ የተባለ የቀንድ ከብት በሽታ ክትባት በነፃ ሰጠ።
Next articleየሕዝብን ድምጽ አክብሮ በመቀበል ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር እንደሚገባ የአማራ ሴቶች ማኅበር ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡