
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የወተት ምርትን 50 በመቶ የሚቀንሰውን ጉርብርብ የተባለ የቀንድ ከብት በሽታ ክትባት በነፃ ሰጠ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጉርብርብ በሽታ (አባ ኬሻ) በቀንድ ከብቶች ላይ የሚከሰት በቫይረስ አማካኝነት
የሚመጣ በሽታ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 13 ነዋሪው አቶ ጥጋቡ ምንዋጋው በወተት ምርት ሥራ ነው የሚተዳደሩት። በጉርብርብ በሽታ የተነሳ
ስድስት ጥጆቻቸውን እንዳጡ ተናግረዋል። በግለሰብ ደረጃ በሽታዉን ለመከላከል አስቸጋሪ መኾኑን የተናገሩት አቶ ጥጋቡ የባሕር
ዳር ዩኒቨርሲቲ ላደረገላቸው የነፃ ሕክምና አመሥግነዋል። ይኹን እንጂ በአካባቢያቸው የእንስሳት ሕክምና ተቋም
እንዲቋቋምላቸው ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ወተት ግብይት የኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር ታደሰ መላኩ የጉርብርብ በሽታ በወተት ልማታቸው ላይ አሉታዊ
ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል። ማኅበራቸው በቀን 3 ሺህ 500 ሊትር ወተት የሚያቀርብ ሲኾን በበሽታው ምክንያት ግን የቀን
ምርታቸውን ወደ 2 ሺህ 500 ዝቅ እንዳደረገባቸው አስረድተዋል። ከአሁን በፊት ሲሰጥ የነበረው ክትባት ወቅቱን ባለመጠበቁ
ውጤታማ እንዳልነበር አስታውቀዋል። አሁን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየሰጠ የሚገኘው ክትባት ግን ወቅቱን ያገናዘበ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህር እንድሪስ አማን (ዶክተር) የጉርብርብ በሽታ የሚከሰተው
በክረምት ወቅት በመኾኑ ክትባቱ አንስሳቱ ከመያዛቸው በፊት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ተገቢ
መኾኑን ነው ዶክተር እንድሪስ ያስገነዘቡት። የጉርብርብ በሽታ የያዛቸው የቀንድ ከብቶች የምግብ ፍላጎታቸውን ይቀንሳል፣
ያስነክሳቸዋል፣ ያከሳቸዋል ብሎም ይገድላቸዋል ብለዋል። በሽታው እስከ 50 በመቶ ድረስ የወተት ምርትን እንደሚቀንስ
መምህሩ አስረድተዋል።
“ዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ በወተት ልማት ለተሰማሩ ማኅበራት ነው ክትባቱን በነፃ መስጠት የፈለገው” ያሉት ዶክተር እንድሪስ
በሂደት ክትባቱን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል። አርቢዎች ሳያስከትቡ አዲስ እንስሳን ከሌላ አካባቢ አምጥተው
ማቀላቀል እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።
ዶክተር እንድሪስ ክትባቱ በየዓመቱ የሚሰጥ ከሆነ በሽታውን ለመከላከል የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m