በከተማዋ ወንጀልን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት የሕዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር መምሪያው ገለጸ፡፡

134

በከተማዋ ወንጀልን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት የሕዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር መምሪያው ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚስተዋሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል የነዋሪዎች ሚና
የጎላ እንደኾነ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡ በመምሪያው የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ኀላፊ ዋና
ኢንስፔክተር ታደሰ ዳኛቸው አልፎ አልፎ ሕጻን በማገት ገንዘብ የመጠየቅ፣ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እና ሌሎች
ወንጀሎች በከተማዋ እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል፡፡
እየተገባደደ ባለው የ2013 በጀት ዓመት የወንጀል ድርጊቶችን በብቃት ለመከላከል ታቅዶ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በወንጀል ድርጊቶች ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥ ስር አውሎ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ በአጥፊዎች ላይ
ውሳኔ እንዲሰጥ የማድረግ ሥራም በስፋት ተሠርቷል፡፡ ጥብቅ ክትትል በማድረግ፣ በድንገተኛ የኬላ ፍተሻና በምርመራ ሥራ
ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በመከታተል በዓመቱ በርካታ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለም
አስታውቀዋል፡፡
በሂደቱም የከተማዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው ኢንስፔክተር ታደሰ የተናገሩት፡፡ በተለይ ወጣቶች ሕዝባዊና
ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ፣ በስፖርታዊ ውድድሮችና ልዩ ልዩ ሁነቶች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው አንስተዋል፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኀብረተሰቡ በባለቤትነት እየሠራ ሲኾን
ለዚህም ከ 100 በላይ ማዕከላት በሕዝብ ድጋፍ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡ በአማካሪ ምክርቤት፣
በግጭት አፈታት ኮሚቴነትና በየአካባቢው የጥበቃ አደረጃጀቶች በመፍጠር ሰፊ ሥራ ሠርተዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ የተካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የኅብረተሰቡ
እገዛ ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስድ በማንሳት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤትና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት በማቋቋም
የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል አገልግሎት አሠራርን ለማሻሻል እየተሠራ ነው፡፡
የወንጀል ድርጊት በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚጎዳው ኅብረተሰቡን በመኾኑ መረጃዎችን ለጸጥታ አካላት በመስጠትና ተሳትፎን
በማጠናከር የፖሊስ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአፍሪካ ከፍተኛው ችግር የእውቀት ብርሀን ማጣት እንደኾነ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ተናገሩ፡፡
Next articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የወተት ምርትን 50 በመቶ የሚቀንሰውን ጉርብርብ የተባለ የቀንድ ከብት በሽታ ክትባት በነፃ ሰጠ።