
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን መርቀው ከፈቱ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ መልክ የተዋቀረውን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) መርቀው ከፍተዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለከፍተኛ አመራሩ የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጥበት ነው። አካዳሚው ከሀገር ተሻግሮ ለመላው አፍሪካ የሚያገለግልም እንደሆነ ተገልጿል።
የአካዳሚው ማስፋፊያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ከቻይና መንግሥት በተገኘ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ነው የተገነባው ተብሏል፡፡
የተቋሙ ስያሜ ሲቀየር ሳይንሳዊ መስፈርቶችን የተከተለ ነው ተብሏል፡፡ ዛሬ የሚመረቀዉ የአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል ማስፋፊያ በውስጡ የስልጠና እና ምርምር ማዕከል የያዘ ነው፡፡ ለባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል በተቀመጠዉ ደረጃ የተገነቡ የተማሪ መኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ መመገቢያ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከል፣ የስፖርት አዳራሽ እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን እንዳሟላ ተገልጿል፡፡
የአካዳሚው መገንባት ከአፍሪካ ሀገራት ለትምህርት ወደ ቻይና የሚደረግን ጉዞ ያስቀራል ተብሏል።
ማዕከሉን የአፍሪካ መሪዎች የልህቀት ማዕከል በማድረግ ዘላቂና የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር የተጀመረውን ጉዞ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት እና በመሪነት ሚና የላቀ የሰው ኃይልን ማፍራት ቀዳሚ ሥራው መሆኑ ተገልጿል።
ዓለማቀፋዊነትን የተላበሱ መሪዎችን በማብቃት የተጀመረውን የሀገር ግንባታ በመደገፍ በአፍሪካ ትልቁ የአመራር የልህቀት ማዕከል ማድረግ ላይ በትኩረትም ይሠራል ተብሏል።
በ2030 የአፍሪካ ቀዳሚው እና ተመራጩ የአመራር የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕይን ሰንቋል።
የቀድሞ የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ ይባል የነበረውን ተቋም ስያሜ የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከል በሚል እንዲሰየም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 15/2013 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
የአካዳሚው የስም ለውጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአመራር ጥያቄዎችን ማሟላት የሚያስችል አቅም ያላቸውን ልሂቃን የሚያፈራ መሆኑን ይገልጻል ተብሏል፡፡
የዕድገት ተኮር አስተሳሰብን የሚያንፀባርቅ የትምህርት ተቋም ማድረግን በሚመጥን እና በሚገልጽ መልኩ በአዲስ እንደተደራጀም ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው ፋንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m