
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ድርጅቶች መሻኮቻ ሳይሆኑ የሁሉም ኅብረተሰብ ሐሳብ እኩል የሚንሸራሸርባቸው መድረኮች መሆን እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብረሃ ገለጹ።
አቶ ገብረጊዮርጊስ እንዳሉት መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ሀብት በመሆናቸው ነጻ ሐሳብ የሚንፀባረቅባቸው፣ ሁሉን በእኩልነት የሚያስተናግዱ መሆን ይገባቸዋል እንጂ ወገንተኛ ሆነው የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ወይም የአንድ ቡድን ሐሳብ አራማጅ መሆን የለባቸውም።
እንደዳይሬክተሩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከተቋቋሙበት ዓላማ፣ ከብሮድካስት ባለስልጣኑ አዋጅ እንዲሁም ሲያቋቁሙ ከገቡት ቃልኪዳን ጋር በሚፃረር መልኩ ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ሕዝብና አገርን ታሳቢ ያላደረገ መረጃን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እያሰራጩ ነው።
የትኛውም መገናኛ ብዙኃን የሚተዳደርበት ደንብ መነሻው መሆን ያለበት የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ የኤዲቶሪያል ፖሊሲው እንዲሁም የብሮድካስት ባለስልጣኑ መተዳደሪያ አዋጅ መሆኑን ያብራሩት አቶ ገብረጊዮርጊስ ‹‹አንዳንድ ሚድያዎች ከዚህ ወጣ በማለት የሚያቀርቡት ዘገባ ሚዛናዊነት የሚጎድለው፣ የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ወይም የአንድ ቡድን ሐሳብን ብቻ ነው›› ብለዋል።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ይዘትና ምንጭ በደንብ ሳያጣሩ መረጃን እንደሚለቁ ኃላፊው ጠቁመው ‹‹እንዲህ ያለው ድርጊት በሕዝብና አገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልባቸው መገንዘብ አለባቸው›› ብለዋል።
መስሪያ ቤታቸው እያንዳንዱ የመገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጨውን ዘገባ የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት ቴክኖሎጂና አሠራር እንዳለው ኃላፊው ገልጸው ከዚህም ባሻገር ባለስልጣኑ ከኅብረተሰቡ የሚደርሰውን ጥቆማ፣ ቅሬታዎችንና አስተያየቶችን መሠረት በማድረግ የመገናኛ ብዙኃኑን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት ቅሬታዎችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹በአንድ ጊዜ ከ100 በላይ የቴሌቪዥንና ከ20 በላይ የራዲዮ ስርጭቶችን ለ24 ሰዓት መቆጣጠር የሚችል የመረጃ ቋት አለን›› ያሉት ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እያንዳንዱን የመገናኛ ብዙኃን በመከታተል ምን ዓይነት ጉድለት አለበት የሚለውን በመለየት ክፍተቱን ለመሙላት ሥራ ላይ መሆኑን በመናገር የመገናኛ ብዙኃኑን አቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ለኢ.ፕ.ድ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሐምሌ 2001 ዓ.ም ጀምሮ ለ126 ጋዜጦች፣ ለ307 መጽሔቶች፣ ለ72 ሬድዮ ጣብያዎች እና ለ29 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ተሰጥቷል፤ ነገር ግን 11 ጋዜጦች እና 14 መጽሔቶች ብቻ በስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሚዲያዎቹ ሥራ ያቋረጡበት ምክንያት በአቅም ማጣትና መሰል ምክንያቶች መሆኑን አመልክተዋል።