
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ሕብረት እየተደረገ ያለውን ድርድር ሱዳን እና ግብጽ እንዲያከብሩ የጸጥታው ምክር ቤትን ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ሕብረት እየተደረገ ያለውን ድርድር ሱዳን እና ግብጽ እንዲያከብሩ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያበረታታ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡
ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በጻፈችው ደብዳቤ በህዳሴ ግድብ ላይ እየተደረጉ ባሉ ድርድሮች የጸጥታው ምክር ቤት እንዲገባ በሱዳንና ግብጽ የቀረበውን ሐሳብ ኢትዮጵያ እንዳልተቀበለችውና ይህም ምክር ቤቱም ከተሰጠው ተልዕኮ ውጭ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ሱዳን እና ግብጽ የጸጥታው ምክር ቤት በድርድሩ ላይ እንዲገባ መፈለጋቸው በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እየተደረገ ያለውን ሂደት ያላገናዘበና በሀገራቱ መካከል ያለውን መተማመን የሚሸረሽር ነው ብላለች፡፡
በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በአፍሪካ ሕብረት የተመራ ድርድር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሱዳንና ግብጽ የሕብረቱን ጥረት ለማዳከም እና ውጤታማ ውይይት እንዳይደረግ ዘጠኝ ጊዜ ሂደቱን እንዳስተጓጎሉ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡
ግብጽና ሱዳን በሚደረጉ ውይይቶች ማደናገሪያ ሐሳቦችን በማንሳት፣ ድርድሩ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እንዲያመራ በማድረግ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳ እያደረጉ መሆኑን አንስቷል፡፡
ሀገራቱ የአረብ ሊግን ወደ ጉዳዩ ጎትተው በማስገባት ሁኔታዎችን የበለጠ በማወሳሰብ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን ሂደት ለማዳፈን መሞከራቸውንም ገልጿል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኘሬዝዳንት ፊሊክስ ቼሲኬዲን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ እያደረጉ ያሉትን እውነተኛ ፣ ቅን እና አበረታች ጥረት እያደናቀፉ እና ተገቢውን ክብር እየሠጡ አለመሆናቸውን ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዳብዳቤው የገለጸው፡፡
በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት በሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር ግብጽ እና ሱዳን በቅን ልቦና እንዲቀጥሉ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያበረታታ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች ብሏል ደብዳቤው በማጠቃለያው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ