
“የወገን ክብር የሀገር ክብር መሆኑን አውቀን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማሳካት ይገባል” የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርኃ ግብር እያካሄደ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚህ ክረምት ችግኝ በመትከል፣ የአረጋውያንን ቤት ተባብሮ በማደስ እና ሌሎችንም የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በመሥራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብር 2 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ መታቀዱን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። ሥራው ”በጎ ፈቃደኝነትን ለመደገፍ እና ለመግባባት” በሚል መሪ መልዕክት ይካሄዳል።
በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ የሰብዓዊ ሥራዎች፣የማኅበረሰባዊ አገልግሎት የትምህርት እና ስልጠና ሥራዎች፣ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት አገልግሎት እና ሌሎች ተግባራት ይከወናሉ ተብሏል።
በ2013 በጀት ዓመት ከ2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ4 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተሠራው ሥራም ከ876 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ የመንግሥት ወጭ ማዳን መቻሉንም የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶች በጎ ፈቃደኛ አገልግሎት ቢሮ ኀላፊ አብርሃም ታደሰ ጠቁመዋል።
የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድም ዛሬ በሚታደሱ 43 ቤቶች ይጀመራል ተብሏል። በዚሁ የክረምት መርኃ ግብር 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዑሽ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ