
“የምርጫውን ሂደት በሰላም እንዲከውን በማድረግ በኩል የመገናኛ ብዙኀን ሚና ጉልህ ነበር” ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሙላቱ ዓለማየሁ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የተካሄደውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሕዝቡ መረጃ ላይ ቆሞ ፓርቲዎችን እንዲመዝን እና የምርጫውን ሂደት በሰላም እንዲከውን በማድረግ በኩል ሁሉም የመገናኛ ብዙኀን ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ የነበራቸው ሚና ጉልህ እንደነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሙላቱ ዓለማየሁ ተናግረዋል::
ሁሉም መገናኛ ብዙኀን የአየር ሰዓት መድበው ውይይት ክርክር ማካሄዳቸው፤ ያሉትን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና ሕብረተሰቡን ስሜት አስተናግደዋል፤ግንዛቤም ፈጥረዋል ይህም ለምርጫው ስኬታማነት ዋጋው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ምርጫ ባልተለመደ መልኩ መገናኛ ብዙኀን ከዚህ በፊት ሊደረስባቸው የማይችሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ በመንቀሳቀሰና መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ በኩል የሰሩት ስራ ትልቅ ነው ያሉት ዶክተር ሙላቱ በተለይ በምርጫው ዕለት ደግሞ 2 ዋና ጉዳዮች ላይ መገናኛ ብዙኀን የሰሯቸው ስራዎች ትልቅ ነበሩ ብለዋል፡፡
ምርጫው እንዴት እየተካሄደ መሆኑን ማሳየት፣ የምርጫ ሕጉን ተከትሎ እየተካሄደ መሆኑን መጠቆም እና እርምት እንዲሰጥ ማድረግ፣ መራጩ አስመራጩና በምርጫ የሚወዳደሩ አካላት የምርጫውን ሂደት እንዴት ታዘቡት የሚሉ ጉዳዮችን በማሳየት በኩል መገናኛ ብዙኀን ኀላፊነታቸውን ተወጥተዋል ነው ያሉት፡፡
መገናኛ ብዙኀን ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ለሁሉም ፓርቲዎች የሰጡት እኩል ድምጽ፣ የጋዜጠኞች ምልከታ በምረጫው ዕለት ሰፊ ግንዛቤ የፈጠረ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በተለይ በምርጫው ዕለት መገናኛ ብዙኀን በቅንጅት እና በትብብር መሥራታቸው ትልቅ ልምድ የሚወሰድበት፣ ለነገ የብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር ለሚሠራው ሥራ መሠረት የጣለ መሆኑን ዶክተር ሙላቱ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ መልካም ተሞክሮ መገናኛ ብዙኀን ብዙ ሊማሩ እና ወደፊት አብረው ሊሠሩ እንደሚገባ ትልቅ ልምድ ሊወሰድበት እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
መገናኛ ብዙኀን የሕዝብ ሀብት እንደመሆናቸው እና ለሕዝብ እንደመቆማቸው ወደፊትም በመረጃ የበለጸገ ዜጋን በመፍጠር ሚናቸው ጉልህ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ