“ከቆመው ድልድይ ሥር የማይቆም ወንዝ አለና ፈፅሞ መቆም አይቻልም”

242
“ከቆመው ድልድይ ሥር የማይቆም ወንዝ አለና ፈፅሞ መቆም አይቻልም”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት 2016 በሀገረ አሜሪካ ተካሂዶ በነበረው የርዕሰ ብሔር ምርጫ ቅድመ መላምቶች ፉርሽ ሲሆኑ በርካቶች ተገርመው ነበር። እንዲያውም ምርጫ ተጠናቆ ውጤት ይፉ በሆነበት ማግስት የሥነ ተግባቦት ልሂቃን ፈጠን ብለው የምርጫ ሂደቱን የሚመለከት አንድ የጥናት ወረቀት ይፋ አድርገው ነበር። በወቅቱ የሚያስገርመው ነገር ልሂቃኑ በወረቀታቸው መግቢያ ላይ ያሰፈሩት አንድ የቅደመ ሐሳብ መንደርደሪያ ነበር።
በ1950ዎቹ አካባቢ አሜሪካ ፓውሎ ሲሞን የሚባል የሙዚቃ አብዮተኛ ነበራት አሉ። ይህ የሙዚቃ አብዮተኛ ታዲያ በአንድ የሙዚቃ አልበሙ ላይ “people hear what they want to hear, and disregarded the rest.” ሲል ተቀኝቶ ነበር። ሐሳቡን በግርድፉ ወደ አማርኛ ስንመልሰው “ሕዝብ የሚያዳምጠው ማዳመጥ የፈለገውን ብቻ ነው” እንደማለት ነው። አጥኝዎቹ ይህንን የፓውሎ ሲሞን ሐሳብ ተውሰው ነበር የጥናት ውጤታቸው መንደርደሪያ ያደረጉት። አዎ ሕዝብ የሚያዳምጠው ማዳመጥ የሚፈልገውን ብቻ ነው። ማዳመጥ የማይፈልገውን ዲስኩር ቢሰማ እንኳን አያዳምጥም። አዳምጦም ዝም አይልም፤ የተመቸውን ይወስናል እንጂ። የሕዝብን ውሳኔ ከመቀበል የተሻለ አማራጭ ደግሞ አይኖርም። ቢኖር እንኳን ጊዜ ጠብቆ የራስን እውነት ለሕዝብ ከመግለጥ የዘለለ ምርጫ አይኖርም “ሕዝብ አይሳሳትም” አይደል የሚባለው።
በወቅቱ የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ እና የጆሮ ቀለብ የነበሩት የያኔው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን በኮንትራት ይመሩ ዘንድ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ ይሁንታውን ችሯቸው ነበርና ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት አቅንተው እና ቃለ መሐላ ፈጽመው ለአራት ዓመታት ወደ መሪነት ዕርካብ ብቅ አሉ።
ከአራት ዓመታት የአሜሪካ ሕዝብ መሪነት በኋላ ደግሞ በ2020 (እ.እ.አ) ለሌላ የአራት ዓመታት የመሪነት ዘመን ኮንትራት ዳግም ወደ ተወዳዳሪነት መድረኩ ብቅ ይሉ ዘንድ ጊዜ አስገደዳቸው። ነገር ግን ይህኛው ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ለተሰናባቹ ሰው ዳግም የመሪነት እድል የሚሰጣቸው አልሆነምና ከመንበረ ስልጣናቸው ይወርዱ ዘንድ ግድ አላቸው።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2020 ፕሬዝዳንታዊ ውድድር ከ70 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ለዳግም መሪነት ይሁንታ ቢቸራቸውም ድምጹን የነፈጋቸው በዛና በሌላ ይተኩ ዘንድ ግድ አላቸው።
70 ሚሊዮን ሕዝብ መርጧቸው እንደነበር ግን ልብ ይሏል። እርግጥ ነው ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዳግም ወደ አሸናፊነት ዕርካብ አለመምጣታቸውን አምኖ መቀበል ሲቸግራቸው አስተውለናል። ሽንፈቱን ለመቀልበስ አማራጭ ያሏቸውን መንገዶች ሁሉ መሞከራቸውም አልቀረም ነበር፤ ምንም እንኳን ትርፉ ቅሌት ብቻ ቢሆንባቸውም። “ሕዝብ አይሳሳትም” ብለን የለ ከመግቢያችን።
ቀደም ሲል ያነሳነውን የተሰናባቹን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጉዳይ ወደ ሀገራችን ወቅታዊ ኑባሬ እናሸጋግረው።
በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስድስተኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ከቀናት በፊት ተካሂዷል። ምርጫውም በሁሉም አካባቢዎች ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን ሂደቱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ጭምር መግለጫ ሰጥተዋል። ምርጫው ለሀገሬው ሕዝብ በሰላም መጠናቀቁ በራሱ አንድ የአሸናፊነት ዜና ተደርጎም ተወስዷል።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ለመታዘብ ፈቃድ ካላገኘባቸው ነጥቦች መካከል አንዱ የምርጫውን ውጤት እኔ ይፋ ላድርግ የሚለውን ጥያቄውን ኢትዮጵያ አለመቀበሏን ተከትሎ መሆኑን እያስታወስን የድህረ ምርጫ ትዝብታችን እንቀጥላለን። ምንም እንኳን በየአካባቢው ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጠት ሂደቱ ሲጠናቀቅ የድምጽ ቆጠራ ተደርጎ ጊዜያዊ ውጤቱ በየምርጫ ጣቢያው ቢለጥፉም የምርጫው የመጨረሻ ውጤት የሚገለጸው ግን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል።
በየምርጫ ጣቢያው የተለጠፉ ጊዜያዊ ውጤቶችን ይዞ በየማኅበራዊ ሚዲያው ማንሸራሸር የምርጫውን ሕጋዊ ሂደት ከመጣሱ በላይ የሚስተዋለው “የአሸናፊ ተሸናፊ ሥነ ልቦና” ከምርጫው መርሆ እና ዓላማ ያፈነገጠ ይመስላል። “ሕዝብ መርጧል፤ ኢትዮጵያ አሸንፋለች” በሚለው ገዥ ሐሳብ የሚስማማ ኢትዮጵያዊ ኹሉ ጊዜያዊውንም ኾነ አጠቃላዩን የምርጫ ውጤት መቀበል ያለበት ከኢትዮጵያ የአሸናፊነት ሚዛን አንፃር ነው። መራጮቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ተመራጮቹም ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ አሸናፊዋም ኢትዮጵያ ናት። በዚህ እሳቤ አብላጫ ድምጽ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ድምጽ ሁሉ አሸንፏል።
“የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ አለው” ሲባል የከረመው የቅድመ ምርጫ መርሆ ለድህረ ምርጫ እሳቤ ዋጋ የማይኖርበት ምክንያት ያለ አይመስልም። ምርጫው ለብሽሽቅ ፖለቲካ ሳይሆን ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ድልድይ ይሆን ዘንድ የተካሄደ ነው። የፈለገውን የመረጠን ሕዝብ ማክበር ስልጣኔ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው።
6ኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ በኩር አይደለም። ምርጫው ልዩ የሚሆነው የሕዝብ ፍላጎት የተስተናገደበት መሆኑ ብቻ ነው። ምርጫው ለኢትዮጵያ የሽግግር ድልድይ ነው። ከዚህ ድልድይ ሥር ግን እንደ ጅረት የማይቋረጥ ሀገር እና ሕዝብ አለ። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገንም ማሰብ ተገቢ ነው።
የዛሬ ማሸነፍ ለነገ ምርጫ ታሪኩ እንጂ ዋስትናው አይደለም። ዛሬ ያልተሳካለት ቢኖር እንኳን በአዲስ መንፈስ እና ወኔ ለነገ እንዲነቃቃ ማበርታት እንጂ መጫን ተገቢ አይሆንም። በዚህ ምርጫ አብላጫ ድምፅ የሚያገኙት ብቻ ሳይሆኑ አነስተኛ ድምፅ የሚያገኙትም በመወዳደራቸው ብቻ አሸናፊዎች ናቸው፡፡
በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ፣ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በትዕግስት ተሻግሮ በአሁኗ ኢትዮጵያ ለምርጫ ውድድር መብቃት አያሌ ጥንካሬዎችን ይጠይቃል፡፡ ከዛሬ ጥንካሬዎች እና ውስንነቶች የተሰበሰበ አቅም እና ልምድ ይዞ ለቀጣዩ ምርጫ የሚመጣ ጠንካራ ተፎካካሪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቃል፡፡ በአጋጣሚ ወደ ውድድር የገባ የፖለቲካ ፓርቲ የለምና አጋጣሚዎች ስላልተመቹ ተስፋ ቆርጦ የሚወጣ ተፎካካሪ ፓርቲ አይኖርም፡፡
ዓላማ ያሰባሰባቸው፣ ራዕይ የመራቸው እና ሕዝብን ያስቀደሙ ኹሉ ከዛሬ ይልቅ ለነገ ትውልድ የጎላ አሻራ ያስቀምጣሉ፡፡ የዛሬ ተፎካካሪዎች ካቆሙት የዲሞክራሲ ድልድይ ሥር ፈጽሞ የማይቆሙ ሀገር እና ትውልድ አሉና ሕይወት ነገም ይቀጥላል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአጣዬ አካባቢ የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት ያከናወናቸውን ሥራዎች እየገመገመ ነው።
Next article“የምርጫውን ሂደት በሰላም እንዲከውን በማድረግ በኩል የመገናኛ ብዙኀን ሚና ጉልህ ነበር” ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሙላቱ ዓለማየሁ