ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ለመሥራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡

141
ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ለመሥራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሥራ እድል ፈጠራን ማበረታታትና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማገዝ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ተፈራረመ። ስምምነቱ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የቆዳ ውጤቶችን በተሻለ ጥራት ለማምረትና የዘርፉን የሥራ እድል ፈጠራ ለማስፋት ያለመ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የዘርፉ ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ሥራ እንዲቀይሩ የሦስት ወራት የተግባር ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታም ይፈጥራል ብለዋል።
በዋናነት ስልጠና በወሰዱባቸው ኢንዱስትሪዎች የሥራ እድል የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርና የተሻለ የፈጠራ ሥራ ያላቸውንም በራሳቸው እንዲንቀሳቀሱ በፋይናንስ እንደሚደግፍ ጠቁመዋል።
ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና ለውጭ ገበያ ጭምር እንዲቀርቡ የማመቻቸት ሥራዎችንም ያካትታል።
በቆዳና የቆዳ ውጤቶችም በጋራ መሥራት የሚያስችለው ስምምነቱ የትምህርት ቤት ቦርሳና ጫማ በስፋት በማምረት ለተማሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በነጻ ለማቅረብ እየተሠራ ያለውን ሥራ መደገፍም በስምምነቱ መካተቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በትምህርት ቤት ቦርሳና ጫማ ማምረት በመጀመሪያው ዙር 1 ሺህ የሥራ እድል ይፈጥራል፤ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በሚሠሩ ሥራዎችም ለ51 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል ብለዋል።
የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዓለማየሁ ኮንዴ መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ፋውንዴሽኑ በሥራ እድል ፈጠራ ወጣቶችን በስልጠናና በፋይናንስ ለመደገፍ የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።
ብሪጅስ የተሰኘው በፋውንዴሽኑ ሥር የሚተገበረው ፕሮግራም ለወጣት አፍሪካዊያን እንደ ሀገራቸው ሁኔታና የሥራ ፖሊሲ የሥራ እድል ፈጠራና ስልጠና በማመቻቸት ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።
ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር የተፈረመው ስምምነትም ምርትና ምርታማነትን በማስፋት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ በኢትዮጵያ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመኖራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ከፓርኮቹ ጋር የማስተሳሰር እድል ያመቻቻል።
የሚሰጣቸው ስልጠናም ከትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ልምድ የሚያገኙበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆን ጥራት ያለው ምርት ማምረት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
ፋውንዴሽኑ ከሚሰጣቸው የተግባር ስልጠና በኋላ ሥራ የሚፈጥሩበት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ድጋፉ ሚኒስቴሩ በመለመላቸውና ብቃታቸውን ባመነባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሰማሩ ወጣቶች ሲሆን በአስፈላጊ ጉዳዮች ኹሉ ትብብር እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
ስምምነቱ ሚኒስቴሩ በዘርፉ የጀመራቸውንና ሊደገፉ የሚገባቸውን ሥራዎች በመደገፍና በማብቃት በዘላቂነት በጋራ መስራት የሚያስችላቸው እንደሆነ መገለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን ከ241 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
Next articleበአጣዬ አካባቢ የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት ያከናወናቸውን ሥራዎች እየገመገመ ነው።