በደቡብ ጎንደር ዞን ከ241 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

157
በደቡብ ጎንደር ዞን ከ241 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ፣ ፎገራና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች ክረምት በገባ ቁጥር ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ የርብ፣ የጉማራ፣ የጓንታና የሌሎች ወንዞች እና የጣና ሐይቅ መሙላት ለአደጋው መከሰት የሚነሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በ2012 ዓ.ም ክረምት ላይ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ እና በጣና ሐይቅ መሙላት በተከሰተ መጥለቅለቅ ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች ቀጥተኛ ተጎጂዎች ሆነዋል፤ ሰብል ወድሟል፤ የቤት እንስሳት ሞተዋል፤ ንብረት ለውድመት መጋለጡም ይታወሳል፡፡ ጉዳቱን ለማካካስ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ልዩ ልዩ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አሚኮ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
በተያዘው ዓመት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ ስዩም አስማረ እንዳሉት በዞኑ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን በዘላቂነት ለመቀነስ እየተሠራ ነው፡፡ የፌዴራል ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ወደ 240 ሚሊዮን ብር ገደማ መድቦ በሦስቱም ወረዳዎች ደለል የማውጣት፣ ቦይ የማስፋፋትና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽንም ወደ 1 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር መድቦ ጎርፍ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በዞኑ ከ241 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን ከጽሕፈት ቤቱ በተገኘ መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡
በዚህ ዓመት ለመሥራት በታቀደው መሠረት ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ስዩም ጠቅሰዋል፡፡
አሚኮም በተለይ በርብና ጉማራ ወንዞች ላይ ማሽኖች ገብተው እየሠሩ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ እየተከናወነ ያለው ሥራ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ስጋትን እንደሚቀንስም ነው የተናገሩት፡፡
በጣና ሐይቅ መሙላት ሊፈጠር የሚችል መጥለቅለቅን ለማስቀረት በተለይም ከጉና ተፋሰስ የሚነሳውን ውኃ በርብ ግድብ በመቀነስና በጨረጨራ ግድብ ለመቆጣጠርና ሌሎች አማራጮችን ለመውሰድ ታስቧል ነው ያሉት፡፡ ሆኖም በዘንድሮው ክረምት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊጥል ስለሚችል የጎርፍ አደጋን ሙሉ በሙሉ ማዳን ስለማይቻል ሕዝቡም የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleቺርቤዋ ሴኒ 15/10/2013 ም.አ(አሚኮ)
Next articleንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ለመሥራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡