
በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኬኒያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የችግኝ ተከላ ሊያከናውን ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኬኒያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የችግኝ ተከላ እንደሚያከናውን አስታወቀ፡፡ በችግኝ ተከላ መርኃግብር ዙሪያ በኤምባሲው የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አምባሳደር ሲራጅ ረሺድ ከኬኒያ የደን ልማት ኃላፊ ጁልየት ካማው ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የሚሲዮኑ ምክትል መሪ የአረንጋዴ አሻራ መርኃግብር በኬንያ ለመተግበር ከኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ጥያቄ በኬንያ መንግሥት ተቀባይነት በማግኘቱ አመስግነዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ችግኝ ተዘጋጅቶ በመጠናቀቁ የችግኝ ተከላ የሚካሄድበትን አካባቢ ተለይቶ የሚሰጥበት፣ ችግኙን ለመትከል ተስማሚ ጊዜ፣ የተዘጋጁ ችግኞችም የተለያዩ አይነቶች በመሆናቸው ለኬንያ ተስማሚ የሚሆኑትን የችግኝ አይነቶች የመለየት ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑ ላይ ገለፃ አድርጓል፡፡
የኬንያ የደን ልማት ኃላፊ ጁልየት ካማው የኢትዮጵያ መንግሥት የአረንጋዴ አሻራን በኬንያ ለማካሄድ አቅዶ ዝግጅት ማጠናቀቁ የሚደነቅና ሀገራቸውም የችግኝ ተካላውን በደስታ የምትቀበል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ናይሮቢ አቅራቢያ ልዩ ስሙ ጎንግ ሂል አካባቢ ከአንድ ሚሊዮን ችግኞች በላይ መትከል የሚቻል መሆኑንና የተወሰኑ ችግኞችንም በከተማዋ ንጎንግ ጎዳና ለመትከል አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ በመጪው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ማካሄድ የሚቻል መሆኑን እንደገለጹ በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ