
“በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለመመለስ እየተሠራ ነው” የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ከተመለከቷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና በሩስያ ያደረጉትን የሥራ ቆይታ የተመለከተ ነበር፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር የሀገራቱን ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት በሚጠናከርበት ዙሪያ መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ደመቀ በሩሲያ ቆይታቸውም ከሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና ባለ ብዙ ወገን ግንኙነት ማስቀጠል በምትችልበት ሁኔታ ላይ ውይይት መድረጉንና ሰለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ገለጻ መደረጉንም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድብ፣ ከትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ሥራ እና ከድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ ሀገራቱ እንደሚደግፉ መግለጻቸውን ቃል ዐቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አየለ መስፍን -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ