
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ከተማ ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ከተማ ገቢያቸው ዝቅተኛ ለኾኑ እና ለችግር
ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች መንግሥት ለሶስተኛ ጊዜ ድጋፍ አድርጓል። በአሽባሪው ትህነግ ምክንያት በሱዳን በስደት የቆዩና
ከስደት የተመለሱም የድጋፉ ተጠቃሚ ኾነዋል።
በሰቲት ሁመራ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪው የሺወንድም ሙሉ መንግሥት ለሶስተኛ ጊዜ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በአካባቢው አሸባሪው ትህነግ በፈጠረው ችግር ምክንያት ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም ከድጋፍ በአጭር ጊዜ
ለመውጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ሌላው በነበረው ችግር ከሀገር እንደወጣና መንግሥት ሕግ በማስከበሩ ወደ ቀየው እንደተመለሰ የነገረን አቶ ተሻገር በላይ
መንግሥት እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ከሱዳን ሲመለሱ ሕዝቡ ደማቅ አቀባበል እንዳደረገላቸውና ወደፊትም
ራሳቸውን እንዲችሉ እገዛ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የሰቲት ሁመራ ከተማ የእርዳታ ማስተባበሪያ ኀላፊ አቶ ተሾመ ስዩም በከተማው ለሶሰተኛ ጊዜ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ
5ሺህ 494 ሰዎች የምግብ እህል እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። በአካባው በአንደኛ ዙር ከ24 ሽህ ሕዝብ
በላይ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡
አቶ ተሾመ በቀጣይም በጥናት ለተለዩ 19ሺህ 156 ሕዝብ ድጋፍ ለማድረስ ዝግጅት መደረጉንም ነግረውናል፡፡
በቀጣይ ከተረጅነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማስቻል መንግሥት እየሠራ መኾኑን የተናገሩት አቶ ተሾመ በቀጣይ በጌጠኛ
ድንጋይ፣ በእርሻና በንግድ ሥራ አደራጅቶ ለማስማራት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
አቶ ተሾመ ኅብረተሰቡ ከተረጅነት ለመላቀቅ ከመንግሥት ጎን በመቆም ጠንክሮ እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ – ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m