“ኢትዮጵያ፡ ምድረ ቀደምት” የትውውቅ መርኃ ግብር በዶሃ ተካሄደ፡፡

125
“ኢትዮጵያ፡ ምድረ ቀደምት” የትውውቅ መርኃ ግብር በዶሃ ተካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዶሃ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ የኢትዮጵያን የባህል እሴቶች እና የቱሪዝም ሃብቶች የሚያስቃኝ “ኢትዮጵያ፡ ምድረ ቀደምት” የተሰኘ መርኃግብር አካሂዷል።
በኳታር ዶሃ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን እና ጋዜጠኞች በዝግጅቱ ተካፍለዋል፡፡
በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በመርኃግብሩ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት እና ነጻነቷን አስከብራ የቆየች ሀገር ብቻም ሳትሆን፣ ለዓለም ያበረከተቻቸው የባህል፣ የታሪክ፣ የሥነ ጥበብ፣ የቋንቋ እና የሌሎች ሀብቶች ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ 13 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን እና ከ12 በላይ የታሪክ መዛግብትን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ያስመዘገበች፤ መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ እና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሀገሪቱን እንዲጎበኝ ጥሪ ቀርቧል።
በመርኃግብሩ የኢትዮጵያን የባህል፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የሥነ ጥበብ እና ሌሎች መስህቦችን የሚያስተዋውቅ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡
የዝግጅቱ ታዳሚዎች ስለ ኢትዮጵያ ግንዛቤ እንደጨበጡ በመግለጽ ሀገሪቱን ለመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። በመርኃግበሩም ደስተኞች መሆናቸውን እንደገለጹ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በዓባይ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛውን አቋምና ተጨባጭ እውነታ ማስረዳት ይገባዋል” በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ጥጋብ በዜ
Next articleበኢትዮጵያ የተካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሥርዓቱን በጠበቀ፣ በሰላምና ተዓማኒነት መጠናቀቁን የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ገለጸ።