
“በዓባይ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛውን አቋምና ተጨባጭ እውነታ ማስረዳት ይገባዋል” በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ጥጋብ በዜ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ ግዮን (ዓባይ) በአዕዋፋት ዝማሬ፣ በእረኞች ዋሽንት እና በጥበብ ሰዎች ዜማ ታጅቦ የሀገሩን ለም አፈር እየጠራረገ ቁልቁል ይፈስሳል፤ በበረሃዋ ግብጽ ሲደርስ ደግሞ በረሃውን ያረሰርሳል፡፡ የኢትዮጵያ ወንዞች በተለያዬ አቅጣጫ የሀገራቸውን አፈር እየሟጠጡ ለባዕድ ሲመግቡ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አፈራቸውን አሳልፈው ከመስጠት ባለፈ እንደ ዓባይ የማያቋርጠውን የጥበብ ቦያቸውን በግብጽና በሱዳን ላይ አሳርፈዋል፡፡ ለሀገራቱ ጥበብን ሰጥተዋል፤ ስልጣኔን አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አመንጭታና አጎልብታ በምትልከው ወንዟና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ከሱዳንና ግብጽ ጋር ረጅም ዘመን የዘለቀ ግንኙነት አላት፡፡
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ጥጋብ በዜ (ዶክተር) ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ረጅም ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው፣ ለዓለም ታላላቅ ጥንታዊ ስልጣኔዎችን አበርከትዋል ብለዋል፡፡ ሀገራቱ ዘመናትን በተሻገረው ግንኙነታቸው መጥፎም መልካምም ጊዜያትን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በዓለም ላይ የግጭት መነሻ ጥቅም ነው ያሉት ዶክተር ጥጋብ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የሚገኙት ሦስቱ ሀገራት በተፋሰሱ የተመሰረቱ ስልጣኔ ያሏቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሀገራቱ ዓባይን መነሻ በማድረግ ብዙ ጊዜ አለመግባባቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ ሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ፣ የንግድና የሃይማኖት ግንኙነት ነበሯቸው ነው ያሉት፡፡ በጥንት ዘመን ጥንታዊ ግብጻዊያን ኢትዮጵያን የዓባይ መነሻ ብቻ ሳይኾን የአማልክቶቻቸው መኖሪያና መፈጠሪያ ቦታ አድርገው ነበር የሚያስቡት፡፡ ግብጻዊያኑ ሁልጊዜም ትኩረታቸው ኢትዮጵያ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ግብጻውያኑ በኢትዮጵያ ዝናብ ሲኾን አስቀድመው በተስፋ ይለመልማሉ፣ ጎርፉ ሲደርስ ይደሰታሉ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ነገራቸው ናትና ብለዋል ዶክተር ጥጋብ፡፡ ሁልጊዜም ተስፋን ከኢትዮጵያ መጠበቃቸው በጥርጣሬ እንዲያይዋት እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይን ጠልፋ ብትጠቀምበት፣ ውኃውስ ቢደርቅብን የሚሉ ስጋቶቸ አብረዋቸው እንደኖሩም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በዘመናት ታሪኳ ተፈጥሮ የቸራትን ሀብት ችግሯን በሚፈታ መንገድ ተጠቅማበት አታውቅም ነው ያሉት፡፡
ዓባይን የመገደብ ጥረቶች ቀደም ብለው መጀመራቸውን ያስታወሱት የታሪክ ምሁሩ በአቅም፣ በመንግሥታት መለዋወጥ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ችግሮች ምክንያት አለመሳካቱን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከዘመናት የሙከራ ጊዜ በኋላ በዚህ ዘመን ተሳክቶላት የታላቁ ህዳሴ ግድብን እየገነባች ትገኛለች፤ ውጤቱንም በቅርቡ እንደምታይ እምነት አለኝ ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን ማለፏንም አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ከውጭ ኃይሎች ጥቃት የተሰነዘረባት ሀገር መኾኗንም ያነሱት ዶክተር ጥጋብ ከሱዳንና ከግብጽ በኩል ግዛት የማስፋፋት ጥቃት ተሰንዝሮባት እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ሀገራቱ ያደረጉት የወረራ ጥረትና ትግል በኢትዮጵያዊያን ትግል መክሸፉን ገልጸዋል፡፡
የሀገራቱ ግንኙነት አንድ ጊዜ ሲሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲቀዘቅዝ የቀጠለ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡ ሀገራቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት መፍትሔው መነጋገርና የችግሮችን መፍቻ ቁልፍ በጋራ ማበጀት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም የያዘችው አቋም ፍትሐዊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብ ለሱዳንና ለግብጽ ይጠቅማል እንጂ ጉዳት አያመጣም ያሉት ምሁሩ ወደ ቀልባቸው ተመልሰው በጋራ ችግሮችን የመፍታትና በጋራ የማደጉን ጥረት መደገፍ ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያዊያንም የድርድር መንገዱን ሳይዘጉ በልማታቸው መጠንከር መቻል አለባቸው ብለዋል፡፡
የግብጽ ሕዝብ በተለያዬ ውሸት እንዲሳሳትና ከግብጽ ፖለቲከኞች ጎን ኾኖ የፖለቲከኞቹን ዓላማ እንዲያሳካ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ዓባይ ከሌለ እነርሱ መኖር እንደማይችሉ ተደርጎ በሁሉም ግብጻዊ እንዲሰርጽ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ግብጻዊያን በሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ስለ ዓባይ እንደሚማሩም አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያን እውነት ለማስተዋወቅና በዓባይ ላይ ያለው እውቀት ከፍ እንዲል ሥርዓተ ትምህርቱ ዓባይን ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ምሁራንም በዓባይ ዙሪያ ጥናት በማድረግ ለመላው ዓለም ማሳወቅ ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ “በዓባይ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛውን አቋምና ተጨባጭ እውነታ ማስረዳት ይገባዋል” ብለዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ እየተደረጉ ያሉ ምርምሮችም ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ