
ከ16ሺህ በላይ የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የግብረ ኃይሉ ቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከስድስት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ወገኖች ላለፉት ወራት በቻግኒ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

ዛሬ ደግሞ ወደ ቡለን፣ወምበራና ድባጤ ወረዳ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የግብረ ኀይሉ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ በትግሉ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ሕይወት እንዲመሩ ከኮማንድ ፖስቱ እና ከቴክኒክ ኮሚቴው ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንም አቶ በትግሉ አስታውሰዋል፡፡
ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ዜጎች መንግሥት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት መደበኛ ሕይወት እንዲመሩ እየሠራ መሆኑንም አቶ በትግሉ ገልጸዋል፡፡ በሂደትም የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ ሲሆን ነዋሪዎች ወደ እርሻና ሌሎች ሥራዎች ይመለሳሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ወደ ቀያቸው የተመለሱት የማንዱራና የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎችም የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ መሆናቸውን እንዳረጋገጡም አቶ በትግሉ ገልጸዋል፡፡ እስከ አሁን የተመለሱትን ጨምሮ ከ50ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ግብረ ኀይሉ እየሠራ እንደኾነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ