የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

222

የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማቱ ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ በላኩት መግለጫ፤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ የሕዝባችንንና የሀገራችንን ደኅንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅማችንን በማረጋገጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ክስተት ስለሆነ መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከፍ ባለ ጨዋነት እና ሥነ ምግባር ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ዳግም ታላቅ ሕዝብ መሆናቸውን አስመስክረዋል ያለው የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማቱ መግለጫ፤ መላው ሕዝብ ያሳየው ከፍተኛ ተሳተፎ፣ ቁርጠኝነት፣ ትዕግስትና ትብብር ለምርጫው ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምዱ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን አንገት ማስደፋቱንም ገልጿል፡፡

የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማት ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻና ገለልተኛ ሆነው የሕዝብን ሰላምና የሀገርን ደኅንነት እንዲያስከብሩ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን እንዲያረጋግጡ የተቀመጠው አቅጣጫና የተሠራው ሥራ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍሬ ማፍራቱን የጠቆመው መግለጫው፤ ተቋማቱ ሁሉንም የምርጫው ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች በገለልተኝነት መርህ እኩል በማገልገላቸው የምርጫው ሂደት የጎላ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የምርጫውን ሂደት ከታዘቡ አካላት እንዲሁም ኅብረተሰቡ ከሰጣቸው ግብረመልሶች መረጋገጡን አመልክቷል፡፡

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ ይቻል ዘንድየፀረ-ሰላምና አሸባሪ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ትርጉም ያለው ተፅእኖ እንዳይኖራቸው በማድረግ ረገድ በቅድመ ዝግጀት ወቅት የተከናወነው ስራ ውጤት አስገኝቷል ያለው መግለጫው፤ ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ደኅንነት ስትራቴጂ ማዘዣ አማካኝነት የሰው ኃይልንና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ክስተቶች ዙሪያ ከአንድ ማዕከል ሁለገብ ክትትልና ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተጨባጭ አቅም መፍጠሩን ጠቁሟል፡፡

ሂደቱ የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማቱ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ተሞክሮ ያገኙበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁሟል፡፡

ምርጫው የተረጋጋች ሀገር እውን በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት የተገነዘቡት የውጭና የውስጥ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ሂደቱን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ በመረጃ መረጋገጡን ተከትሎ ጥምረት ፈጥረው የተንቀሳቀሱት የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማት የተለያዩ ሴራዎችን ሲያከሽፉ እንደነበር መግለጫው አስታውሷል፡፡

በምርጫው ሂደትም የደኅንነትና የጸጥታ መዋቅሩ አመራሮችና አባላቱ ለሕዝብና ለሀገር ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት ሌት ተቀን በመላው ሀገሪቱ በመሰማራት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሀገር ፍቅር መንፈስ በመወጣታቸው የጎላ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ጉልህ ሚና ማበርከቱን ጠቅሷል፡፡

ከሕዝብ አብራክ ተገኝተው ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት ለከፈሉት መስዋዕትነትም ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት ይገባቸዋል ብሏል፡፡

በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከምንም በላይ ለሀገር ህልውና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም ለሕዝብ ውሳኔ እንደሚገዙ በማረጋገጥ ኢትዮጵያ የተደቀነባትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተና በጋራ ለመመከት በሚያስችል የአብሮነት መንፈስ የድምጽ መስጠቱ ሂደት እክል እንዳያጋጥመው ያደረጉት ጥረትም ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ውጤቱ በይፋ በሚገለጽበት ወቅትም የሕዝብን ድምጽ በማክበር ለጋራ ሀገር ግንባታ በትብብር መሥራቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ መሆኑን ለማረጋገጥ የተሰማሩ ታዛቢዎች፣ እንዲሁም መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ለማድረስ የተሰማሩ የመገናኛ ብዙኃንና በየደረጃው የሚገኝ የመንግሥት መዋቅር የድምጽ አሰጣጡ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ
ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የገለጸው የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማት መግለጫ፤ የተጣለባቸውን ግዴታ በላቀ ስነምግባር በመወጣታቸው ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማቱ በየትኛውም ጊዜና ወቅት የሀገራችንን እና የሕዝባችንን ጸጥታና ደኅንነት የሚጎዱ ከወጭም ይሁን ከውስጥ የሚቃጡ ማናቸውንም ጥቃቶችና ስጋቶች ከመላው ሕዝባችን ጋር በመቀናጀት ለመመከት ያለንን የወትሮ ዝግጁነት በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን ብለዋል፡፡

“ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!”
የፌደራልና የክልል የደኅንነትና ጸጥታ ተቋማት
ሰኔ 15፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Previous articleበቤልጂየም፣ሉግዘምበርግ እና ሆላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጫናን የሚቃወም ሰልፍ አካሄዱ።
Next article“የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ” “የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከል” በሚል እንዲሰየም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጸደቀ።