
በአዲስ አበባ በልደታ ክፍለ ከተማ የድምጽ አሰጣጡ እንደቀጠለ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ከመምረጥ ባለፈም አረንጓዴ አሻራቸውን ሲያሳርፉ ውለዋል።
በአዲስ አበባ በልደታ ክፍለ ከተማ በዚህ ሰዓት ለመምረጥ ሰልፍ ይዘው ያገኛቸው የአሚኮ ዘጋቢ መራጮች ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመውሰድ የዛሬው የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ትልቅ ድል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ለኢትዮጵያ ነገ ስንል በሰላም ውጤቱን መቀበል ላይ ልዩነት ሊኖረን አይገባንም” ነው ያሉት መራጮቹ፡፡
በምርጫ ጣቢያው አሁን ድረስ ረጃጃም ሰልፎች ይታያሉ። በጣቢያው ውስጥ ላይ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን አለመሆን እና ዝናብ መኖር ሂደቱ በሰዓቱ እንዳይከናወን አድርጓል ሲሉም የምርጫ አስፈጻሚዎች ነግረውኛል።
በልደታ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 3 ምርጫ ጣቢያ 32 ውስጥ በሚገኙት 4 የምርጫ ጣቢያዎች በአሁኑ ሰዓት የድምጽ መስጠት ሂደቱ ቀጥሏል።
ምርጫው ሲጠናቀቅም ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ በተሰጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ውጤትን በቆጠራ አረጋግጦ ለምርጫ ክልል ለመላክ የቆጠራ ሥራው ይጀመራል፡፡
የምርጫ አስተዳደር ደግሞ ውጤቱ ከሁሉም ማእከሎች አሰባስቦና አደራጅቶ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጊዜያዊ ውጤቱም ነገ በየምርጫ ጣቢዎቹ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከልደታ ክፍለ ከተማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ