
የባሕር ዳር ምርጫ ክልል የድምጽ መስጠት ሂደት ችግር አለማጋጠሙን የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ምርጫ ክልል ድምጽ መስጠት ሂደት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በስኬት እየተካሄደ መሆኑን የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ ወይዘሮ ማኅደር አዳሙ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አስተባባሪዋ መረጃ በምርጫ ክልሉ ባሉ 144 የምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስም ሆነ የጸጥታ ችግር አላጋጠመም፡፡
በጎ ፈቃደኛ ባለመገኘቱ በምርጫ ጣቢያዎች ከመራጮች የሚወከሉ ቅሬታ ሰሚዎች ለማቋቋም የተደረገው ጥረት ካለመሳካቱ ጋር የተያያዘ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ መነሳቱን አስተባባሪዋ አንስተዋል፡፡ ችግሩ በድምጽ መስጠት ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረውም አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡
ቅሬታዎች ሲኖሩም በጋራ እየተፈቱ ድምጽ መስጠት ሂደቱ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከሌላ አካል የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን ወይዘሮ ማኅደር ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ