
“ሰላማዊ ሆኖ መጥቶ ሕዝቡ በሰላም ወደ ቤቱ ሲመለስ ደስ ይለናል” ምክትል ኮማንደር ጥላሁን ካሳ
“የምትጠባ ህጻን ከቤት ትቸ ነው ውጭ ያደርኩት” ዋና ኢንስፔክተር ሻሼ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ደምቢያ ቆላድባ ከተማ በጸጥታ ሥራ ላይ ተሠማርተው ያገኘናቸው ዋና ኢንስፔክተር ሻሼ ሁሉም ሥራ የየራሱ ሊከፈልለት የሚያስችል መስዋእትነት ይኖረዋል ነው ያሉት። ለሕዝብ ተብሎ የሚከፈል ዋጋ እንዳለም አስረድተዋል። የራስን ምቾት ችላ ብሎ ለሕዝብ ራስን አሳልፎ መስጠት ሲቻል ከበሬታን ያስገኛል ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ሻሼ የፖሊስነት ሥራ ለራስ ሳይኾን ለሕዝብ ሰላም ቅድሚያ መስጠትን ከሚሹ ሙያዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
በተለይ እንደሰሞኑ ምርጫን የመሰለ ሀገራዊ ጉዳይ ሲመጣ ከቤት ውጭ ማደር፤ ከአካባቢ ርቆ መሄድ ግድ ሊል ይችላል ብለውናል። ዋና ኢንስፔክተር ሻሼ አራስ ቢኾኑም ልጃቸውን ከቤት ትተው የምርጫ ቁሳቁስ ሲጠብቁ እንዳደሩ ነው የነገሩን፡፡
“ባለቤቴም ባጋጣሚ ፖሊስ በመሆኑ የሚገርምህ ቤት ልጆችን ትተን ነው እዚህ የሕዝብን ሰላም እያስጠበቅን ያለነው” ብለዋል። ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን እየሠሩ እንደኾነ የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተሯ እስከ መስዋእትነት ሕዝቡን ለመጠበቅ መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።
ምክትል ኮማንደር ጥላሁን ካሳ በምሥራቅ ደምቢያ ቆላድባ ከተማ የምርጫ ጣቢያ ሀ ጸጥታን እያስጠበቁ ነበር ያገኘናቸው፡፡ እርካታቸው ሕዝቡ በሰላም መጥቶ መርጦ በሰላም ሲመለስ ማየት እንደኾነ የነገሩን ምክትል ኮማንደር ጥላሁን ዛሬ ከተለያዩ አካባቢዎች ስምሪት ላይ ካሉ ባልደረቦቻቸው ጋር መረጃ እየተለዋወጡ እየሠሩ መሆኑን ገልጸውልናል።
ኢትዮጵያ ሰላም ውላ ሰላም እንድታድር ሳይታክቱ እየሠሩ ላሉ የጸጥታ አባላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ፈረደ ሽታ – ከቆላ ድባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ