
በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫዉ በሰላም እየተከናወነ መኾኑን የመንዝ ማማ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ማማ ወረዳ የምርጫ ክልል በሚገኙ 67 የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫዉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እየተከናወነ መኾኑን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። በምርጫ ክልሉ 94 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ፤ 67 በመንዝ ማማ እና 27 በመንዝ ላሎ ምድር ወረዳዎች የሚገኙ ናቸው።
አሚኮ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ ምርጫው በሰላም እየተከናወነ ይገኛል። የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ግርማ ገብረሐና የምርጫው ሒደት በሁሉም ጣቢያዎች ሰላማዊ ኾኖ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ኅብረተሰቡ በሰላም መርጦ በሰላም ወደተለመደ ሥራው እንዲሠማራ የፀጥታ ኀይሉ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ እንደኾነም ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ከድምፅ አሰጣጡ መጠናቀቅ በኋላም ቢኾን አሁን ያለው ሰላም እንዲቀጥል የጋራ ሥራ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የምርጫ ክልሉ 27 ጣቢያዎች የሚገኙበት የመንዝ ላሎ ወረዳም በተመሳሳይ ሰላማዊ ምርጫ እያከናወነ መኾኑን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ገልጿል። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው ጌጤነህ ለአሚኮ እንደተናገሩት ምርጫዉ በሰላም እየተከናወነ ነው።
በሞላሌ ምርጫ ክልል ከ52 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ድምፅ ለመስጠት ካርድ አውጥተዋል፤ በ94 ምርጫ ጣቢያዎችም ድምፅ የመስጠቱ ሒደት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ እንደቀጠለ ነው።
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ – ከመንዝ ማማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ